ሁሉም ሠራተኛና አመራር በመደመር መንፈስ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር በትጋት መስራት አለበት

ሁሉም ሠራተኛና አመራር በመደመር መንፈስ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር በትጋት መስራት አለበት

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሁሉም ሠራተኛና አመራር በመደመር መንፈስ በተሰማራበት መስክ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ለሰንደቅ ዓላማ ክብር በትጋት መስራት እንዳለበት የተቋሙ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞችና አመራሮች “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን!” በሚል መሪ ቃል 19ኛውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተቋም ደረጃ አክብረዋል።

ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን በአንድነት በአድዋ የሕይወት ዋጋ ጭምር በመክፈል ሰንደቅ ዓላማቸውን በክብር ከፍ በማድረግ የነጻነት ቀንዲል የሆነች ሀገር አውርሰውናል፡፡

የመደመር መንግስትም ሰንደቅ ዓላማዋን በክብር ከፍ የሚያደርጉና የበለጸገችና አንድነቷ የተጠበቀች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን አቅዶ በጊዜ የለኝም መንፈስ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን በመዘከር እና ከሥራችን ጋር በማስተሳሰር ለሀገር ሉዓላዊነትና ሁለንተናዊ እድገት በአንድነት ለመሥራት ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር አሸብር ለዚህም የተቋሙ ሠራተኛና አመራር በሰንደቅ ዓላማው ፊት የገባውን ቃል ወደ ተግባር በመለወጥ ከወትሮው በተለዬ መልኩ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አንድነቷ የተከበረችና የታፈረች ሀገር ለመጨው ትውልድ ለማስተላለፊ ልዩነቶችን በውበት ይዞ በአንድ የጋራ ዓርማ ጥላ ሥር በመደመር መንፈስ መሥራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሠንደቅ ዓላማ ቀን ከዋና መ/ቤት በተጨማሪ በሁሉም የተቋሙ ፕሮጀክቶች፣ ሪጅናችና ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በታላቅ ድምቀት ተክብሯል።

Scroll to Top