የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ በ2019 በጀት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ተቋማዊ አፈፃፀምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ማከናወኑን አስታወቀ፡፡
የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግመዋል፡፡
በዘርፉ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ብዙአየሁ አክሊሉ እንደገለፁት በሩብ ዓመቱ ተቋሙን ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማሸጋገርና አስተማማኝ የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ የሲስተም መቋረጦች እንዳያጋጥሙ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የዲጂታል ፕሮግራም መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አቶ ፈለቀ አፈወርቅ እንደተናገሩት ባለፉት ሦስት ወራት ተቋሙን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ የአሰራር ሥርዓቶች ተዘርግተዋል፡፡

የሳፕ (SAP) የአቅም ግንባታና የዲጂታል ግዥ (E-Procurement) ፕሮጀክቶች የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራዎች በጊዜ ሰሌዳቸው መሰረት ተጠናቀው ክፍያ መፈፀሙን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ፈለቀ ገለፃ የሰነድ አስተዳደር እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ የመስፈርት ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡
የሳይበር ደህንነት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አድማሱ በበኩላቸው ባለፉት ሦስት ወራት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሳይበር ደህንነት ትግበራ ፕሮፖዛል ተገምግሞ ለሥራ ተቋራጩ ግብረ መልስና የማሻሻያ አስተያየት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ለኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሳይበር ደህንነት መስፈርቶች ተዘጋጅተው ለሥራ ተቋራጩ መላካቸውንም አብራርተዋል።
በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ጽዮን በቀለ እንደገለፁት የዘርፉ አብዛኛዎቹ ሥራዎች ካለፈው በጀት ዓመት የተሸጋገሩ እና በግዥ ሂደት መዘግየት ምክንያት ሲንከባለሉ የቆዩ ናቸው።

የግዥ መዘግየቶችን ለመቅረፍ በተደረገው መዋቅራዊ ማሻሻያ የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ግዥዎች ተለይተው እንዲከናወኑ መደረጉ የዘርፉን ሥራዎች ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የዋናው መሰብሰቢያ አዳራሽ ዕድሳት ከሲቪል፣ አርክቴክቸር፣ ኤሌክትሪካል፣ ሜካኒካል ምህንድስና እንዲሁም ከሳይበር እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፈርቶች ጋር ተቀናጅቶ የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው አዳራሹን ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት በዘርፉ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን የገለፁት ወ/ሮ ጽዮን በቀጣይም የታቀዱትን ሥራዎች በፍጥነት ወደ መሬት በማውረድ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።




