የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚያከናውናቸው የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም ሠራተኛ እና የሥራ መሪ ኃላፊነት ወስዶ መስራት እንዳለበት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አሳሰቡ።
ተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን ከሠራተኞችና ሥራ መረዎች ጋር በመሆን ገምግሟል።
በበጀት ዓመቱ በኦፕሬሽንና በፕሮጀክት ግንባታ አፈፃጸም እንዲሁም በሰው ኃይል ልማት፣ በፋይናንስ፣ በኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ በዲጂታላይዜሽንና በንብረት አስተዳደር የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ተወካይ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያለውአይቀር ማንደፍሮ ቀርቧል፡፡

በሪፖርቱ በገቢ አሰባሰብ፣ የኃይል ማንጫ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ኦፕሬሽን ማስገባት፣ በራስ አቅም ፕሮጀክቶችን የማከናወን አቅም እያደገ መምጣት፣ በኃይል ማመንጨትና ሽያጭ እንዲሁም የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን በማስጠበቅ በኩል በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ከኃይል መሰረት ልማት ግንባታ አንጻር በኃይል ማመንጫ ዘርፍ አምስት ፕሮጀክቶች እና በኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ዘርፉ 31 ፕሮጀክቶች በተለያዩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
የተመረተ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከማሳደግ አንጻር በ2017 በጀት ዓመት 29 ሺህ 480 ጊጋ ዋት ሰዓት ምርት እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ያለውአይቀር በ2018 በጀት ዓመት 35 ሺህ 734 ጊጋ ዋት ሰዓት ማመንጨት መቻሉንና ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ21 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልፀዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 477 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን የጠቆሙት ተወካይ ሥራ አስፈፃሚው በ2017 በጀት ዓመት ከተገኘው 337 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ የ41 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በነዳጅ እጥረትና በጸጥታ ችግር ውስጥ ሆኖ የተመዘገቡ ዓመታዊ አፈጻጸሞች ተቋሙን ከነበረበት ኪሳራ በማውጣት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርፍ እንዲያስመዘግብ ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አዲሱን የካሳ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር፣ የግንባታ ሥራቸው የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በወቅቱ የካፒታላይዜሽን ሥራ ለመስራት እና ከተቋሙ አቅምና ከሀገራዊ ፍላጎት ጋር በተጣጣመ መንገድ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት ለማከናወን እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም ለማጠናከር ቀጣይ ሥራ እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ላይ በተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በሚመለከታቸው የዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በግምገማው ላይ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ ተግባራት እንደ ሀገር የነበረውን 15 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ያልበለጠ የኢነርጂ ምርት ወደ 35 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ማሳደግ ተችሏል፡፡

ሆኖም ከፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያልተሻገርናቸውን ችግሮች ለመፍታትና ብክነትን ለማስወገድ ኦዲት በማድረግ እንዲሁም የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን በማጠናከር ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል።
ሁሉም ሠራተኛና የሥራ መሪ የእኔንት ስሜትን በመላበስና ሌት ተቀን በመስራት የተቋሙን መልካም ስምና ዝና በመጠበቅ በኩል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጠቅሰዋል።
እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ ሀገሪቱ ቀጣይነት ባለው ዕድገት ውስጥ የምትገኝ በመሆኑና በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየገቡ በመሆናቸው ሀብትን በአግባቡ በማስተዳደርና አሰራሩን በማዘመን በኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል።
በቀጣይ በጀት ዓመት እያንዳንዷ ኪሎ ዋት ስዓት ሳትባክን ወደ ገንዘብ ለመለወጥና የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ አፋጣኝ ውሳኔዎችን ለመስጠት መረባረብም ይገባል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በብዙ ችግሮች ውስጥ በማለፍ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።
አሰራርን በማዘመንና ብክነትን በማስወገድ ኢትዮጵያን ብርሃን ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ሁሉም ሠራተኛ ድርሻውን በመወጣት አሻራ ማሳረፍ እንዳለበት አቅጣጫ ሰጥተዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
