የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 119 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
በተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስና የሰው ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደገለፁት ገቢው የተሰበሰበው ከኃይል ሽያጭ፣ ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ፣ ከባለፈው ዓመት ከዞረ የኃይል ሽያጭ እና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች እንዲሁም ካለፈው በጀት ዓመት የዞረ ተሰብሳቢ ሂሳብ ነው፡፡
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 129 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 119 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 92 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት የሰበሰበው ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 57 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማጠናከር፣ ወቅቱን የጠበቀ ክትትል በማድረግ እና የኃይል ሽያጩን ከሚያከናውነው የማርኬቲንግ ክፍል እንዲሁም ከደንበኞች ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ በመሰራቱ በገቢ አሰባሰብ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመደበኛ ወጪዎች እንኳ ከራሱ ገቢ ሰብስቦ መሸፈን አይችልም ነበር ያሉት አቶ ደመረ አሁን ላይ ግን የገቢ አሰባሰቡን በማዘመንና በማጠናከር ከዕዳ ወደ ምንዳ መሸጋገሩን ገልፀዋል።
ተቋሙ ከነበረበት 168 በመቶ ኪሳራ ወጥቶ በበጀት ዓመቱ ያልተጣራ 39 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልፀዋል።
ለዚህ ስኬት መገኘትም የተቋሙን የሥራ አመራር ቦርድና መንግሥትን ጨምሮ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ድርሻ የጎላ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይ የተቋሙን የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ወጪ በመቀነስ ብሎም ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጎልበት የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ደመረ አብራርተዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በሰጡት አቅጣጫ ከንብረት አስተዳደር፣ ከገቢ አሰባሰብና ከሰው ሀብት ልማት ጋር ተያይዞ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ግልጽ አሰራር በመዘርጋት መሥራት ይገባል ብለዋል።

የተቋሙን ሀብትና ንብረት በአግባቡ እንዲጠበቁ ችግሮችን ተከታትሎ መፍታትና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ተቋሙ ከ7 ሺህ 700 በላይ ሠራተኞችን የያዘ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ተቋማዊ ባህልን ማሻሻል ይገባል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኘው ገቢ እና ያልተጣራ ትርፍ ከተቋሙ ሀብትና አቅም አንጻር ሲታይ የሚያኩራራ አለመሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር አሸብር ወጪን በመቀነስ፣ ብክነትን በማስወገድና የገቢ አማራጮችን በማስፋት ቀጣይነት ያለው ውጤት ማስመዝገብ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከገቢ አሰባሰብ፣ ከንብረት አስተዳደር፣ ከሰው ሀብት ልማት እና ከግዥ ሂደቶች ጋር ተያይዞ ያሉ አሰራሮችን በመፈተሽ የተሻለ ተቋማዊ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም የሥራ መሪ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል።




