በኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ የታቀዱ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት በማጠናቀቅ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አሳሰቡ።
በዘርፉ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም በተሳታፊዎች ከፕሮጀክት አስተዳደር፣ ከግብዓት አቅርቦት፣ ከግዥ ሰንሰለት እና ከሰው ሀብት አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት የዘርፉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ እንደገለፁት የአፈፃፀም መዘግየት በሚታይባቸው ፕሮጀክቶች ላይ አስቸኳይ ውሳኔ በመስጠት፣ በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል።
የኢንጂነሪንግ ቢሮው የአማካሪነት ሚናውን እየተወጣ በመሆኑ ለውጭ አማካሪ ሊከፈል የሚችለውን ወጪ በማስቀረት ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
እንደ ኢንጂነር ውድነህ ገለፃ ወደ ፕሮጀክት ትግበራ ከመገባቱ በፊት አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በትኩረት መከናወን አለባቸው።

በዘርፉ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማሳደግ፣ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን በማጠናከር እንዲሁም ለችግሮች መፍትሔ በመስጠት የፕሮጀክት መዘግየቶችን ማስወገድ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
በዘርፉ ግምገማ ላይ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት በተለያዩ ምክንያቶች በሥራ ተቋራጮች በኩል ተቋርጠው የቀሩ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ በማስረከብ ረገድ አበረታች ሥራዎች ተሰርተዋል።
ዘርፉን በሠው ኃይልና በቴክኖሎጂ በማደራጀት ከተቋሙ ውጪ ወጥቶ የመስራት ዕቅዱን ለማሳካት አሁን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ነው ያነሱት።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት እና በውጭ የሥራ ተቋራጮች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ የሚያስችሉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች መሰራት አለባቸው።
ዘርፉ ወደ ፊት የተሟላ ሥራ ተቋራጭ ለመሆን ከያዘው ዕቅድ አንፃር ትርፋማ መሆን እንዳለበትና ለዚህም የተቋሙ ከፍተኛ አመራር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።







