ተቋሙ በራስ አቅም የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች እያደጉ መጥተዋል

ተቋሙ በራስ አቅም የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች እያደጉ መጥተዋል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መምሪያ በራስ አቅም የሚያከናውናቸው የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን በተቋሙ የኢንጂነሪንግ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ።

ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር ውድነህ የማነ የዘርፉን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ተቋሙ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት የሚያሳድጉ በርካታ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን እያከናወነ ይገኛል።

ዘርፉ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ተቋማዊ አቅምና ሀገራዊ ጥሪት እንዲፈጠር በአማካሪነት እና በሥራ ተቋራጭነት በመሳተፍ  በርካታ የኃይል መሰረተ ልማቶችን አጠናቆ ወደ ኦፕሬሽን ማስገባቱን አስታውቀዋል።

​እንደ ኢንጂነር ውድነህ ገለፃ ለመጀመሪያ ጊዜ በአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሙሉ አማካሪነት እንዲሁም በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተባባሪ አማካሪነት  መሳተፍ ተችሏል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ በሚገኙ 24 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቶች ላይ በሥራ ተቋራጭነትና በአማካሪነት እየተሳተፈ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ዘርፉ ከተቋሙ ፕሮጀክቶች ባለፈ ለ9 ሌሎች የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በአማካሪነት እንዲሁም የገዳ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክትን በሥራ ተቋራጭነት ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

​በበጀት ዓመቱ በራስ ኃይል ሲከናወኑ የቆዩትን የደጀን-ደብረ- ማርቆስ፣ የበቆጂና የደብረታቦር ማከፋፈያ ጣቢያዎችንና ማስተላለፊያ መስመሮችን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ኦፕሬሽን መግባታቸውን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም የመቀሌ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የትራንስፎርመር እና የቤይ መትከል፣ የአዲስ ሴንተር ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ እና የቢሺፍቱ የኬብል መቅበር ሥራዎች እና የጂማ-አባ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጄክቶች የተሻለ አፈጻጸም እንደተመዘገበባቸው አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት፣ የወሰን ማስከበር መዘግየት፣ የጸጥታ ሁኔታዎች፣ የታቀዱ የጥናት ሰነዶች በጊዜ አለመጠናቀቅ፣ የሥራ ማከናወኛ መሣሪያዎች እጥረት እና የግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት መዘገየት ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተገልጿል።

​በበጀት ዓመቱ የጸጥታ ችግርና የነዳጅ እጥረት ውስጥ ሆኖ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም እና የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት በኩል የተሻሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።

​የግንባታ ዕቃዎችን በወቅቱ ሳይት አለመድረስ፣ ወደ አገልግሎት የገቡ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት አጠናቆ አለመዝጋት እንዲሁም በፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ትርፋማ አለመሆን በዘርፉ የታዩ ክፍተቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።

Scroll to Top