ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸው ተገለፀ

ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸው ተገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2018 በጀት ዓመት ያስቀመጣቸውን ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ የኃይል ማከፋፈያና ማስተላለፊያ ግንባታ እንዲሁም የኦፕሬሽን ሥራዎች ማከናወኑን አስታወቀ።

በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ደስታለም ኃይሉ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ የብሔራዊ ግሪድ አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ፣ የኃይል ብክነትን ለመቀነስ እና የኦፕሬሽን ልህቀትን ለማስፈን ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል።

በበጀት ዓመቱ 31 ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታቅዶ 18ቱ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5 ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ተጠናቀው ወደ ኦፕሬሽን መግባቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የበቆጂ-ደብረታቦር ባለ 230 ኪሎ ቮልት ፕሮጀክት፣ የደጀን-ደብረማርቆስ-አሸጎዳ-ደሴ-ሆርማት ፕሮጀክት፣ የመቱ-ማሻ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ፕሮጀክት፣ የብሔራዊ ኤሌክትሪሲቲ ግሪድ ደቡባዊ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆኑት ወላይታ ሶዶ II እና አርባምንጭ I እና II፣ የጅማ-አባ ባለ132 ኪሎ ቮልት ፕሮጀክት፣ የገንዳ አርባ (ቡልቡላ) አግሮ ኢንደስትሪ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ተጠናቀው ወደ ኦፕሬሽን መግባታቸውን አብራርተዋል።

እንደ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የጥገናና የኦፕሬሽን መረጃዎች የሚያዙበት እና በግሪዱ ላይ የሚከሰቱ ሁኔታዎችን ለመከታተል የሚያስችል መተግበሪያ በራስ አቅም በማበልፀግ በትግበራ ሒደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በ18 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የጂ.አይ.ኤስ ብሬከር ቅየራ ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

የፋይበር ኦፕቲክስ፣ የአርቲዩና የስካዳ ጥገናዎችን በማድረግ የመረጃ ታይነትን(Data Visibility) ከ75 ወደ 100 ጣቢያዎች ማሳደግ መቻሉንም አብራርተዋል::

የግሪድ ደህንነትን ከማጠናከር አኳያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ውሃ በአግባቡ ለመጠቀም የኔትወርክ ማስተካከያ መሰራቱን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎሎች እና የነዳጅ እጥረት በፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኢንጂነር ደስታለም ገለፃ በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለ2 ሺህ 407 ለዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።

በቀረበው የዘርፉ ሪፖርት ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷባቸዋል።

በዘርፉ ግምገማ የማጠቃለያ ሀሰባ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም በማሻሻል እንዲሁም አቅም ያላቸውን የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮችን በማሳተፍ የኃይል ተደራሽነቱ ላይ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል።

የፕሮጀክት አመራር ችግሮችን በመቅረፍ ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ከውጫዊ ፈተናዎች ይልቅ የውስጥ ችግሮችን በመፍታትና የድጋፍና ክትትል ሥርዓቱን በማጠናከር መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የኦፕሬሽን ሥራዎችን ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ አቅም በመጠቀም የአሰራር ሥርዓታቸውን ለማዘመን ከጊዜ ጋር መሮጥ ይገባል።

Scroll to Top