በዓለም ላይ ያሉ ውጤታማ የኃይል ማመንጫ አሰራሮችን በመቅሰም በጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አሳሰቡ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይሄን የተናገሩት ተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍን ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት መድረክ ላይ ነው።
በዘርፉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በቀረበው ሪፖርት ላይ ከፕሮጀክት አስተዳደር፣ ከኃይል ማመንጨት አቅም፣ ከግድብ ደህንነት፣ ከፋይናንስ አጠቃቀም እና ከመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባዋል።

በዘርፉ የግምገማ ማጠቃለያ ላይ አቅጣጫ ያስቀመጡት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር በበጀት ዓመቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጨምሮ የአሰላ እና የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት በኩል ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ተቋሙ አዳዲስ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባሻገር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ዋነኛ ተልዕኮው መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በማሻሻል፣ የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማዘመን፣ ብክነትን በመቀነስ እንዲሁም የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን በማጠናከር በኩል በትኩረት መሥራት ይገባል።

የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በዕቅድ ላይ ተመስርቶ ከማደስና መልሶ ከመገንባት ባለፈ የኃይል ስብጥሩን ለማስፋት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የግድብ ደህንነት እና የፕሮጀክት አስተዳደር ሥራዎችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን እንቅፋት የሚሆኑ አሰራሮችን ለይቶ መፍታት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በዘርፉ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው ለሚሰሩ ባለሙያዎች ድጋፍ ለማድረግና ለጥያቄዎቻቸው አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አመራሩ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል።
በፕሮጀክቶች እና በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ዕቃዎችን በአግባቡ መዝግቦ በማደራጀት ብክነትን የመቀነስ ሥራ በትኩረት መከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።
ከመረጃ አያያዝ፣ ከሪፖርት አቀራረብ፣ ከቅንጅታዊ አሰራር እና ከሀብት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መኖራቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ የተስተዋሉትን እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም አመራር ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።










