የተቋሙን ስትራቴጂካዊ ግቦች በስኬት ለማሳካትም ሆነ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን፣ ዘመናዊና ጠንካራ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት መሠረታዊና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቀላጠፈ ደረጃውን የጠበቀና ውጤታማ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችለውን አራተኛ ዙር የከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ሥልጠና ለፕሮጀክት ዳይሬክተሮችና ሥራ አስኪያጆች መስጠት ጀምሯል።
በዕለቱ ሥልጠናውን የሰጡት በተቋሙ የአሰላ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅና አሰልጣኝ ኢንጂነር ጌቱ ጌቱ ያደቴ እንደገለጹት ይህ ሥልጠና ተቋሙ በፕሮጀክት አስተዳደር ረገድ የሚያጋጥሙትን መዋቅራዊና አሰራር ነክ ፈተናዎች በዘላቂነት በመሻገር፣ ከልማዳዊ አሰራር ወደ ተመራጭና ዘመናዊ የፕሮጀክት መሪነት ሥርዓት እንዲሸጋገር አቅም ይፈጥራል።
ተቋሙ ቀደም ሲል ይጠቀምባቸው የነበሩት የፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር ልምዶች የተወሳሰቡ በመሆናቸው በፕሮጀክቶች አፈጻጸም የጊዜና የበጀት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ማነቆዎችን ይፈጥሩ እንደነበር ያወሱት ኢንጂነር ጌቱ አሁን ባለው ነባራዊና ፈጣን ሁነቶች ውስጥ የአስተዳደር ዘይቤውን ወደ ዘመናዊና የተቀናጀ ሥርዓት ማሸጋገር ለተቋሙ ሁለንተናዊ ስኬት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ሥልጠናው ዋና ዋና የፕሮጀክት ምዕራፎችንና ዓለም አቀፍ አሰራሮችን የሚያካትት ሲሆን በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት በሀገሪቱ የልማት ስትራቴጂ ውስጥ የሚጫወተው ውሳኔ ሰጪ ሚና ከግምት ውስጥ በመግባት ለፕሮጀክቶቹ ስኬታማነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ ይገኛል።
በሥልጠናው ወቅት ተሳታፊዎች በንድፈ-ሐሳብ ብቻ ሳይወሰኑ በተግባራዊ ልምምዶችና በቡድን ውይይት የሚያልፉ ሲሆን የቀደሙ አፈጻጸሞችን፣ የተገኙ ተሞክሮዎችንና የተቋሙን የፕሮጀክት መሪነት ሞዴል ምዘና መሠረት በማድረግ ልምድ የሚቀስሙ ይሆናል።


ይህ አቅምን የመገንባት እንቅስቃሴ የተቋሙን የፕሮጀክት አመራርና የሥራ ሂደት ወደ ላቀ ዘመናዊ ደረጃ በማሸጋገር፤ የፕሮጀክቶችን ጥራት፣ የጊዜ ገደብና የሀብት አጠቃቀም ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ታምኖበታል።


