በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ፈጣን መልሶ ጥገና ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የቴክኒካል ድጋፍ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አበባው ያለው እንደገለፁት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የተደረጉት የአደጋ ጊዜ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች (Emergency Restoration Tower) በተለያየ ምክንያት የሚወድቁ የብረት ምሰሶዎችን በአጭር ጊዜ በመተካት የኃይል መቋረጥን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንሱ ናቸው።
በተጨማሪም የብረት ምሰሶዎቹ የተጨናነቁ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን አነስተኛ የኃይል ፍሰት ወደሚገኝባቸው ለማዘዋወርና ከአገልግሎት ውጭ የነበሩትን በፍጥነት ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት የእንጨት ምሶሶዎች እንደነበሩ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
የኤሌክትሪክ ገመዱ ከመሬት ጋር እንዳይነካካ ለማድረግም ከ18 እስከ 20 የሚደርሱ ፖሎችን መትከል ይጠይቅ እንደነበር አብራርተዋል።
በአንፃሩ በአሁኑ ወቅት በሙከራ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋሉት የአደጋ ጊዜ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች በደጋፊ ገመዶች (Anchor Wire) በቀላሉ የሚገጣጠሙ በመሆናቸው የተቋረጠውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሚያስችሉ አስረድተዋል።
እንደ አቶ አበባው ገለፃ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎቹ ወደ ሥራ መግባት የተቋሙን አሰራር ከማዘመን ባለፈ የጥገና ሠራተኞችን ለጉዳት እንዳይጋለጡ በማድረግ ደህንነታቸውን አስተማማኝ ያደርጋል።
የአደጋ ጊዜ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን በስፋት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ሥልጠና ከሁሉም ሪጅኖች ለተውጣጡ መሐንዲሶች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና ለማስተባበሪያ ቡድን አባላት መሰጠቱንም ገልፀዋል።
በሞጆ አካባቢ በተካሄደው የተግባር ሥልጠና ወቅት ባለሙያዎቹ ባደረጉት ተደጋጋሚ ልምምድ የአንድ ጊዜያዊ ምሰሶ ተከላ ጊዜን ከግማሽ ቀን በላይ ይወስድ ከነበረበት ዝቅ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
በመምሪያው የኃይል ማስተላለፊያዎች የቴክኒካል ድጋፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን አባተ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ከቢሾፍቱ ወደ ቆቃ እና ሁርሶ እንዲሁም ከገላን ወደ ሞጆ በሚሄዱ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የተከሰቱና እስከ 7 ቀናት ሊወስዱ ይችሉ የነበሩ የኃይል መቋረጦችን የአደጋ ጊዜ የብረት ምሰሶዎችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ጭነት ማመጣጠን ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።


የቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ለማስፋትና በኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ላይ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት የጥገና ምላሽ የመስጫ ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ በተደረጉ ጥናቶች መሰረት ለሪጅኖቹ ማዕከል የሆኑ ቦታዎች መመረጣቸውን ተናግረዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ቴክኖሎጂውን በተለያዩ የቮልቴጅ መጠኖች ጥቅም ላይ ለማዋል ተጨማሪ ግዢዎችን ለመፈፀም የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገም ይገኛል።
በቀጣይም ከዕቃ አቅራቢው ኤስ.ቢ.ቢ (SBB) ኩባንያ ጋር በመተባበር በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም በኃይል መቋረጥ እና በመልሶ አገልግሎት የማስጀመር የአስተዳደር ሥርዓቶች(Power Outage and Restoration Management System) ዙሪያ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ለመስጠት መታቀዱንም ጠቅሰዋል።

