የኃይል መሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል፤

የኃይል መሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል፤

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሰራር ሥርዓቶች በመተግበር ለውጥ መምጣቱን የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በጽ/ቤቱ የአስተዳደራዊ ጉዳዮች ሥራ አስኪያጅ ግርማ ግዛቸው (ዶ/ር) እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ለዋና ሥራ አሰፈጻሚ የሚቀርቡ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ተፈጻሚነት ለማሻሻል፣ ተቋማዊ እና የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የፖሊሲ፣ ፕሮሰስና ለውጥ ማኔጅመንት ተግባራትን በማከናወን ስትራቴጅካዊ ግቦችን ለማሳካት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 5 ሪጅኖች 1 ሺህ 411 የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን በማኅበረሰቡ ለማስጠበቅ ታቅዶ በ1 ሺህ 279 ምሰሶዎች ላይ ተፈጻሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ 23 የብረት ምሰሶዎች በጸጥታ፣ በተፈጥሮ እና በሌሎች ጉዳዮች የወደቁ ሲሆን ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ46 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የብረት ምሰሶዎችን በማስጠበቅ ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ኪሳራ ማዳን ተችሏል።

በ36 የብረት ምሰሶዎች ላይ ሊፈጸም የነበረ የስርቆት ሙከራ በአካባቢው ማኅበረሰብ እና በጸጥታ አካላት ትብብር መክሸፉን የገለጹት ዶ/ር ግርማ በአጥፊዎቹ ላይም እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት እና እስከ 20 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ቅጣት መተላለፉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመትም በ8 ሪጅኖች በ18 የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች 2 ሺህ 49 የብረት ምሰሶዎችን ለማስጠበቅ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።

ከጸጥታና ከፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት ከ15 ነጥብ 33 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተቋሙን ንብረቶች ማስመለስ መቻሉንም ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በተቋሙ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለመፍታትና የአሰራር ሥርዓቶችን ለማስተዳደር እንዲሁም የፖሊሲ ዝግጅት ለመምራት የሚያስችል መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለከፍተኛ ማኔጅመንት ማቅረብ ተችሏል።

ተቋማዊ ባህልን ለማጠናከር የሚያስችል ሰነድ የማዘጋጀት እንዲሁም በ7 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና በ18 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የካይዘን ፍልስፍናን ለመተግበር ለ232 የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም ተቋማዊ ሰነዶችን በማዕከላዊነት የሚያስተዳድር ሥርዓት በራስ አቅም የበለፀገ ሲሆን አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

Scroll to Top