ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የተቋሙን ጥቅምና ገጽታ የሚያስጠብቁ ሥራዎችን ተከናውነዋል

ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የተቋሙን ጥቅምና ገጽታ የሚያስጠብቁ ሥራዎችን ተከናውነዋል

በ2018 በጀት ዓመት ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የተቋሙን ጥቅምና ገጽታ የሚያስጠብቁ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮምፕሊያንስና ገቨርናንስ ዘርፍ ገለጸ፡፡

የዘርፉሥራ አስፈጻሚ ተወካይ ወ/ሮ መስከረም በቀለ እንደገለጹት የተቋሙን ስትራቴጅክ ዕቅድ መሰረት በማድረግ የተቋሙን ገጽታ ከመገንባት፣ ብልሹ አሰራሮችን ከመከላከል፣ የተቋሙን ጥቅም ከማስጠበቅ፣ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን ከማስፈን እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 10 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መጠን ባላቸው 355 የፍትሐብሄር እና 57 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መጠን ባላቸው 37 የሥራ ክርክር መዝገቦች ላይ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

4 ቢሊዮን ብር መጠን ባላቸው 156 መዝገቦች የፍትሐብሔር መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ከ2 ነጥብ 78 ቢሊዮን ብር በላይ ለተቋሙ መወሰኑን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ ውሳኔ ከተሰጠባቸውና 31 ነጥብ 86 ሚሊዮን ብር መጠን ካላቸው 16 የሥራ ክርክር መዝገቦች ከ25 ነጥብ 84 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን አብራርተዋል።

6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መጠን ያላቸው 199 መዝገቦች ወደ ቀጣይ በጀት ዓመት መሸጋገራቸውንም ተናግረዋል።

እንደ ወ/ሮ መስከረም ገለጻ በበጀት ዓመቱ በ29 የወንጀል መዝገቦች በ38 ተከሳሾች ላይ ከአንድ ዓመት እስከ አስር ዓመት የእስራት ቅጣት በፍ/ቤቶች ማስወሰን ተችሏል።

ከተለያዩ ውሎች፣ ከመግባቢያ ሰነዶች፣ ከፖሊሲዎችና መመሪያዎች ጋር በተያያዘ በ502 ጉዳዩች ላይ የሕግ ምክር አገልግሎት በመስጠት የተቋሙ አሰራሮች ሕግና ሥርዓትን ተከትለው እንዲፈጸሙ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በበጀት ዓመቱ በሥራ ቦታ ሥነ-ምግባር እንዲሁም በስልታዊ ኮሙዩኒኬሽን ጽንሰ ኃሳብና አስፈላጊነት ዙሪያ ለተቋሙ የሥራ መሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

54 የሙስና ጥቆማዎችን በመቀበል የ36ቱ ምርመራ ተጠናቆ ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች መመራቱንና የቀሪ 18 ጥቆማዎች ደግሞ በምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ መመሪያዎችን በመፈተሽና የማስተካከያ ምክረ-ሀሳቦችን ከማቅረብ ጎን ለጎን በተደረጉ ክትትሎች ከከ35 ነጥብ 41 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

አዲስ በተዘጋጀዉ ዲጂታል የሀብት ምዝገባ ስርአት (EARS) መሰረት በአጠቃላይ 700 የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ስለመደረጉም ተናግረዋል።

የተለያዩ የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎችንና የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም የተቋሙን ገጽታ ለመገንባት የተለያዩ ሥራዎች ስለመከናወናቸውም አንስተዋል፡፡

በተቋሙ ለሚሰሩ 51 ሴቶች የአመራር ክህሎትን ማሳደጊያ እንዲሁም ለ110 ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር የግንዘቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ወ/ሮ መስከረም አብራርተዋል።

የሰው ኃይል እጥረት፣ ሥልጠና በተያዘለት ጊዜ ያለማግኘት እና የሥራ ኃላፊዎች ለሚቀርብላቸው የመረጃ ጥያቄዎች በሚፈለገው ጊዜና ጥራት መረጃ አለመስጠት በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የተቋሙን ጥቅሞች ከሚጎዱ ብልሹ አሰራሮች በመራቅ እንዲሁም ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የተቋሙን መልካም ስም ለመገንባት ሁሉም ተቋማዊ አምባሳደርነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Scroll to Top