በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ፈጣን መልሶ ጥገና ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ የአደጋ ጊዜ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች (Emergency Restoration Towers) በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ተደርገዋል።
ይህ ቴክኖሎጂ ምን ዓይነት ጥቅሞችን ይዞ መጥቷል?
- ፈጣን መልሶ ጥገና
ቀደም ሲል በአደጋ ወቅት ከ18 እስከ 20 የሚደርሱ የእንጨት ምሶሶዎችን መትከል ይጠይቅ የነበረ ሲሆን አዲሶቹ ምሰሶዎች ግን በደጋፊ ገመዶች (Anchor Wire) በቀላሉ የሚገጣጠሙ በመሆናቸው የተቋረጠውን መስመር በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት ያስችላሉ።
- የኃይል ጭነት ማመጣጠን
የተጨናነቁ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን አነስተኛ የኃይል ፍሰት ወደሚገኝባቸው በማዘዋወር ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ አካባቢዎች በፍጥነት ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ያደርጋል።
- የሠራተኞች ደህንነትና የአሰራር ዘመናዊነት
የጥገና ሠራተኞችን ለጉዳት እንዳይጋለጡ በማድረግ ደህንነታቸውን አስተማማኝ ያደርጋል።
በተግባር ምን ውጤት ተገኘ?
በሞጆ አካባቢ በተደረገ ሥልጠናና ልምምድ ባለሙያዎቹ የምሰሶ ተከላ ጊዜን ከግማሽ ቀን በታች ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ከቢሾፍቱ ወደ ቆቃ እና ሁርሶ እንዲሁም ከገላን ወደ ሞጆ በሚሄዱ ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመሮች ላይ ተከሰተው እስከ 7 ቀናት ሊወስዱ ይችሉ የነበሩ የኃይል መቋረጦችን በእነዚህ ምሰሶዎች አማካኝነት ፈጣን መፍትሔ መስጠት ተችሏል።
በቀጣይ ምን ታስቧል?
ቴክኖሎጂውን ወደ ሁሉም ሪጅኖች ለማስፋትና የጥገና ምላሽ ጊዜን ይበልጥ ለመቀነስ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ።