በሥራ ላይ ደህንነት እና ጤንነት  ዙሪያ ሥልጠና እየተሰጠ ነው

በሥራ ላይ ደህንነት እና ጤንነት  ዙሪያ ሥልጠና እየተሰጠ ነው

በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና ሪጅኖች ለተመደቡ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤና አስተባባሪ መሐንዲሶች በሥራ ላይ ደህንነት ላይ ያተኮረ ሥልጠና መስጠት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ላይ ደህንነትና ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ኮርሳ ተሬሳ እንደገለፁት ሥልጠናው መሐንዲሶቹ በተመደቡባቸው የሥራ ቦታዎች ላይ በሚኖራቸው የሥራ ላይ ደህንነት እና ጤንነት ክትትልና ቁጥጥር ላይ ያላቸውን የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ ያለመ ነው።

ሥልጠናው ባለሙያዎቹ በሥራ ላይ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ስጋቶችን በመለየት መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱን  ነው የገለፁት።

እንደ አቶ ኮርሳ ገለፃ ከተቋሙ ስፋት አንፃር  የተመደቡት ባለሙያዎች በቂ ባይሆኑም በቀጣይ የሰው ኃይሉን በማጠናከር የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ታቅዷል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ጋር ተያይዞ የተቋሙን ሠራተኞች አስተሳሰብ ለመቀየር የሚያስችሉ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ለመስጠት  መታቀዱንም አብራርተዋል።

የሥራ ላይ ደህንነት የአንድ ዘርፍ ወይም ሥራ አመራር ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆነ የገለፁት ሥራ አስኪያጁ የሠራተኞችን ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ ሁሉም የተቋሙ የሥራ መሪና ሠራተኛ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሥልጠናው በሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦች፣ በዘርፉ ህጋዊ ማዕቀፎች፣ በዓለም አቀፍ የደህንነት ዕድገት ታሪክ፣ በአደጋ ስጋቶች መለየትና ምዘና እና በድንገተኛ አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ አሰጣጥ ዕቅድ አዘገጃጀት እንዲሁም በሪፖርት አቀራረብ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

Scroll to Top