የፕሮጀክቱን የሲቪል ሥራ አፈፃፀም 17 ከመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው

የፕሮጀክቱን የሲቪል ሥራ አፈፃፀም 17 ከመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው

የደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የፕሮጀክት የሲቪል ሥራ አፈፃፀምን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ 17 ከመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ  የተመራ ቡድን የፕሮጀክቱን ግንባታ ሲጎበኝ ሥራ አስኪያጁ አብዱ ኪያር እንደተናገሩት በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ግንባታው የተጀመረው የማከፋፈያ ጣቢያ የፕሮጀክት አፈፃፀም 12 በመቶ ደርሷል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ሳይቱን ለግንባታ ዝግጁ በማድረግ የመሬት ቆረጣና የአፈር ማንሳት፣ የአፈር መንሸተት መከላከያ ግንብ ግንባታ፣ የመኖሪያ ቤት መሠረት ግንባታ እና ኮለን የማቆምና ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

63 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮችን በቦታቸው የማስቀመጥ ሥራ መጠናቀቁን የሳይት ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

የተቋሙ የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ በበኩላቸው የማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት በደሴና አካባቢዋ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልፀዋል። ይህም ተቋሙ በሁሉም አካባቢዎች እያደረገ ያለውን የልማት ተደራሽነትን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ግንባታው የሚገነባበት ቦታ ጥቁር አፈር በመሆኑ ተጨማሪ የመሬት ቆረጣና አፈር የማንሳት ሥራ ማስፈለጉን የተናገሩት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሥራው ቀድሞ ከታሰበው ውጭ ያጋጠመ በመሆኑ የተወሰነ መጓተት ማስከተሉን ጠቁመዋል፡፡

ሥራውን በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን በቀሪ ጊዜያት ውስጥ ጠዋትና ማታ መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫን አስቀምጠዋል።

በጉብኝቱ ላይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ጨምሮ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መምሪያ ዳይሬክተር ሰለሞን ኃይለጊዮርጊስ፣ የኢንጂነሪንግ ሱፐርቪዥንና ኮንትራት አስተዳደር መምሪያ ዳይሬክተር ግርማ ዘለቀ፣ በዘርፉ የግዥና ፋይናንስ መምሪያ ተወካይ ዳይሬክተር ሙሉቀን ዮሴፍ ተገኝተዋል፡፡

የደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ወጪ ሙሉ ለሙሉ በተቋሙ የሚሸፈን ሲሆን የግንባታ ሥራውን የተቋሙ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መምሪያ የአማካሪነትና የቁጥጥር ስራዎችን ደግሞ የተቋሙ የኢንጂነሪንግ ሱፐርቪዥንና ኮንትራት አስተዳደር መምሪያ በጋራ ይሰሩታል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top