
በሁርሶ ባለ 230/33/15 ኪሎ ቮልት ማከፋፊያ ጣቢያ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ መቆጣጠሪያዎችን በዘመናዊ መቆጣጠሪያዎች በመቀየር ጣቢያውን የማዘመን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ተወካይ ገለፁ።
ተወካዩ አቶ ናትናኤል ምንተስኖት እንደገለጹት ማከፋፈያ ጣቢያው ላይ የነበሩ መቆጣጠሪያዎች ለብዙ ዓመት ያገለገሉ ከመሆናቸው ባሻገር ዘመኑን የዋጁ አልነበሩም።
ይህም የማስተላለፊያ መስመሮቹ ከጣቢያው እየራቁ ሲሄዱ እና በመስመሮቹ ላይ ችግሮች ሲፈጠሩ በቀላሉ ቮልቴጅ እንዲዋዥቅ በማድረግ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ያስከትሉ እንደነበር ተወካዩ ገልጸዋል።
አሁን የተቀየሩት በጋዝ የሚሰሩት የጂ አይ ኤስ መቆጣጠሪያዎች በጣቢያው እና በመስመሮቹ ላይ ችግሮች ሲከሰቱ ቀድመው በማሳወቅ መቆጣጠሪያው በራሱ ችግሩን እንዲለይና እርምጃ እንዲወስድ በማድረግ በጣቢያው እና በመሳሪያዎቹ ላይ ችግር እንዳይከሰት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።
በጣቢያው የሚከናወነው የመቆጣጠሪያ መሳሪዎች ቅየራ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪ የኮሙዩኒኬሽን እና ሌሎች መሳሪያዎችን በመግጠም ከስካዳ ስርዓቱ ጋር ለማገናኘት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ጣቢያው 125 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች እና 50 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር ያለው ሲሆን እስከ 180 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም አለው።
እንደ ተወካዩ ገለጻ ማከፋፈያ ጣቢያው ከቆቃ እና ከአይሻ ሁለት በ230 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር ኃይል ተቀብሎ ለድሬዳዋ ፣ ሀረር፣ ጅግጅጋ ለአዲጋላ እና ጅቡቲ በአጠቃላይ ለምስራቁ የሀገራችን ክፍል ዋንኛ የኃይል ምንጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


