የጫካን ፕሮጀክት የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ እስከ ነሐሴ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

የጫካን ፕሮጀክት የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ እስከ ነሐሴ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

በጫካ ፕሮጀክት የተጀመረውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፊያ ጣቢያ ግንባታ እስከ ነሐሴ 2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፊያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ ገለጸ፡፡

በዘርፉ የፕሮግራም 1 ፕሮጀክት አስተዳደር 3 ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ የትናየት ይመር እንደገለጹት በጫካ ፓርክ ፕሮጀክት ክልል የሚያልፉ የማስተላለፊያ መስመሮችን ከፓርኩ ማስተር ፕላን ጋር በማጣጣም መስመሮችን የማዛወርና በጊዜያዊነት ለኃይል አቅርቦት የሚያገለግል የተንቀሳቃሽ ማከፋፊያ ጣቢያ ተከላ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የግንባታ ሥራው በጫካ ፓርክ አቋርጦ የሚያልፈውን የኮተቤ – ቤላ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር የማዛወር ሥራ የሚይዝ ነው፡፡

ግንባታው የ3 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የመሬት ውስጥና የ0 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የአየር ላይ (ኦቨር ሄድ) መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የ0 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ቅየራ ሥራዎችን እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ የትናየት ገለፃ ከኮተቤ – አያት ከተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ 0 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩን በመሬት ውስጥ የመቀየር ሥራ በተጓዳኝ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የኮተቤ – አዲስ ኢስት ባለ 132 ኪሎ ቮልት ጥምር የማስተላለፊያ መስመርን የማዛወር ሥራ እንደሚከናወን የገለጹት ወ/ሮ የትናየት ይህም የ1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የመሬት ውስጥ እና የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የአየር ላይ መስመር ዝርጋታ ሥራን እንደሚያካትት አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለኮተቤ – ቤላ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የመስመር ማዛወር ሥራ የሚያስፈልጉ ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ተመርተው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከቤላ እስከ ጫካ ተንቀሳቃሽ ማከፋፊያ ጣቢያ ያለው የ0 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር የተከላ እና ፍተሻ ሥራ መጠናቀቁንና የተንቀሳቃሽ ማከፋፊያ ጣቢያው የፍተሻ ሥራ መጀመሩን ሥራ አስኪያጇ አስታውቀዋል፡፡

ለኮተቤ – አዲስ ኢስት መስመር ማዛወር ከሚያስፈልጉ 6 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች የአራቱ የተከላ ሥራ ተጠናቆ ኮንዳክተር የመዘርጋት ስራ መጀመሩን እንዲሁም ቀሪ ሁለት ምሰሶዎች የከፍተኛ መስመር ኃይል ማቋረጥ ስለሚጠይቁ መሬት ላይ ቀድመው መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራ TBEA በተባለ የቻይና ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑን ወ/ሮ የትናየት ተናግረዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ በተቋሙ የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ በኩል የተንቀሳሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ሲቪል ስራ እንዲሁም ከኮተቤ ጫካ በነባር ምሰሶዎች ላይ የጥገና እና የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

አሁን ባለው ፕሮጀክቱ የሥራ ወሰን መሰረት የመሬት ውስጥ መስመር ዝርጋታ ስራ ላይ የክረምቱ የአየር ሁኔታ ተፅዕኖ የማያሳድር ከሆነ ሥራዎችን እስከ ነሐሴ 2016 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጭ 370 ሚሊየን ብር የሚገመት ሲሆን ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸፈን ይሆናል፡፡

Scroll to Top