የኃይል ሽያጭ ታሪፍን ለማሻሻል የቀረበ ምክረ-ሃሳብ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

የኃይል ሽያጭ ታሪፍን ለማሻሻል የቀረበ ምክረ-ሃሳብ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት  የኃይል ሽያጭ ታሪፍን ለማሻሻል በጋራ ባዘጋጁት ምክረ-ሃሳብ ከተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአድዋ ሙዚዬም የስብሰባ አዳራሽ ምክክር ጀምረዋል።

የምክክር መድረኩ በኢነርጂ ዘርፉ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ፣ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም በኤሌክትሪክ አገልግሎት የታሪፍ ጥናት ላይ ያተኮረ ነው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ  እንደተናገሩት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ኃይል ለማመንጨትና ለማሰራጨት ኃላፊነት የተሰጣቸው ባለፈቃድ መስሪያ ቤቶች ያቀረቡትን የብሔራዊ ግሪድ ታሪፍ ገምግሞ የውሳኔ ሃሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል።

ባለሥልጣኑ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ፣ በተጠቃሚውና በመንግሥት በኩል ያሉ ፍላጎቶችን በህግ አግባብና በታሪፍ መገምገሚያ መስፈርት መሠረት ሚዛናዊ ውሳኔ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሶስቱንም አካላት ፍላጎት አስጠብቆ ለማስቀጠል አዳጋች የሆኑ የዘርፉ ዕድገት ማነቆዎች በርካታ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ ባለፉት ሁለት ዓመታት መከለስ የነበረበት የኤሌክትሪክ ታሪፍ ያለ ማሻሻያ በመቆየቱ ሳቢያ ኃይል አቅራቢ ተቋማቱን ለኪሳራ የዳረገና በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ ሆኖ ተገኝቷል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት ወ/ሮ ሳህረላ ይሁን እንጂ ለኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የታሪፍ ማሻሻያ ባለመደረጉ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የፋይናንስ እጥረት እንዲገጥማቸውና ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ እንዲዘፈቁ  ምክንያት እንዳደረጋቸው እንረዳለን ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የታሪፍ ጥናት አዘጋጅተው ባቀረቡት መሠረት የታሪፍ ቅድመ ግምገማ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የታሪፍ ማሻሻያው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ፤ አስቸኳይ ጥገናዎችን ለማካሔድ፤ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና የኃይል አማራጮችን ለማስፋት እንዲሁም የኃይል ኤክስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የሚዲያ አካላት የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊነትን በበቂ ሁኔታ በማስረዳትና ለማህበረሰቡ በማስገንዘብ የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የሁለቱ ተቋማት የመሰረተ ልማትና የፋይናንስ ቁመናን የተመለከቱ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በቀጣይ ቀናትም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተመሳሳይ ምክክር በማድረግ ተጨማሪ ግብዓት የማሰባሰብ ሥራ የሚሰራ ይሆናል።

Scroll to Top