የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያዘጋጁት ረቂቅ የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ክለሳ የኢነርጂ ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች አስታወቁ።
ተቋማቱ የኃይል ሽያጭ ታሪፍን ለማሻሻል በጋራ ባዘጋጁት ምክረ-ሃሳብ ከሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአድዋ ሙዚየም የስብሰባ አዳራሽ ምክክር አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ተቋማዊ ገፅታና ለታሪፍ ክለሳው መነሻ የሆኑትን ጉዳዮች ለመድረኩ ያቀረቡት የተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከውሃ 4 ሺህ 820 ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 404 ሜጋ ዋት እና ከእንፋሎት 32 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨች ትገኛለች።
የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ከ20 ሺህ 200 በላይ ኪሎ ሜትር መድረሱን የጠቀሱት አቶ አንዱዓለም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ 3ኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት የምታስተዳድር ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።
እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ አጠቃላይ ሀብቱ 672 ቢሊየን ብር ቢደርስም 367 ቢሊየን ብሩ በዕዳ የተመዘገበ ነው።
አነስተኛ የሀገር ውስጥ የነፍስ ወከፍ የኤሌክትሪክ ፍጆታ፣ ዝቅተኛ የኃይል ተደራሽነትና የማመንጨት አቅም፣ አስተማማኝ ያልሆነ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም ያልተቀላጠፈ አሰራር የኃይል ልማት ዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውን ነው የገለፁት።
ለዘመናት የተከማቸውን ዕዳ ማቃለል፣ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እና ተጠናቀው አገልግሎት የሚሰጡበትን አሰራር መዘርጋት ከተተገበሩ የሪፎርም ተግባራት መካከል እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል።
ተቋሙ በ2021 ዓ.ም የግል ባለሃብቱን በማሳተፍ የኃይል ማመንጨት አቅምን ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ያብራሩት ሥራ አስፈፃሚው ከውሃ 6 ሺህ 166 ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 2 ሺህ 255 ሜጋ ዋት፣ ከእንፋሎት 1 ሺህ 500 ሜጋ ዋት እንዲሁም ከፀሐይ 975 ሜጋዋት ተጨማሪ ኃይል ለማግኘት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ በ2023 ዓ.ም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ወደ 30 ሺህ 345 ኪሎ ሜትር እንዲሁም የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ብዛት ወደ 323 ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል።
እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ ለኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ200 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ከ25 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ያስፈልገዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው በበኩላቸው የኃይል ሽያጭ ታሪፉ ከ2011 ዓ.ም ከተሻሻለ በኋላ በየዓመቱ በአማካይ ከ350 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ መሰራት ካለባቸው ሥራዎች አንፃር አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
እንደ አቶ እሱባለው ገለፃ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ከ 8 ሺህ አምስት መቶ በላይ ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እስከ 27 ዓመት ሊወስድ ይችላል።
ተቋሙ ኪሳራ ላይ ነው ባይባልም ዓመታዊ የተጣራ ትርፉ ግን አራት ትራንስፎርመሮችን እንኳ መግዛት የማያስችል መሆኑን ነው ያብራሩት።
የታሪፍ ማሻሻያው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል፣ ተደራሽነቱን ለማስፋት፣ ሀገራዊ እና የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ነው የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች አመልክተዋል።
“ከካርቦን ልቀት የፀዳ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል!”





