የጥናቱን ምክረ ሀሳቦች ከነባራዊ ሁኔታው ጋር አስማምቶ መተግበር ይገባል

የጥናቱን ምክረ ሀሳቦች ከነባራዊ ሁኔታው ጋር አስማምቶ መተግበር ይገባል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን በተከናወነው ጥናት የተመላከቱ ምክረ ሀሳቦችን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር አስማምቶ መተግበር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን ያከናወነውን ጥናት ለተቋሙ አመራሮች በስካይ ላይት ሆቴል አቅርቧል፡፡

ጥናቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የኃይል ኤክስፖርት ታሪፍ ማስተካከያ ማዕቀፍ እንዲሁም የመንግስትና የግል አጋርነት የኃይል ግዢ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራትን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም የአሁኑ የታሪፍ ሥርዓት፣ የደቡብ ኮሪያና የሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እንዲሁም የተቋሙ የፋይናንስ ችግሮችና በቀጣይ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊተገበሩ የሚገቡ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ታሪፍ የተቋሙን የፋይናንስ ዘላቂነት፣ የኢንቨስትመንት አቅምን፣ ቀጣናዊ የኃይል ንግድን፣ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን፣ ማህበራዊ ፍትሃዊነትን እና የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ የረጅም ጊዜ ልማት የሚነካ  መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

ስለሆነም የድርድር ሥርዓቱን ለማዘመን በድርድር ወቅት ሊተገብሯቸው የሚችሉትን የተዋቀረ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት፣ የትንተና አመክንዮ፣ የስሌት ቴምፕሌቶችን፣ የስጋት ክፍፍል መሣሪያዎችን፣ የድርድር ቼክሊስቶችን እና የውል ድንጋጌዎችም ቀርበዋል።

በቀረበው ጥናት ላይ ከተወያዮች ጥያቄዎችና አስተያዬቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎበታል።

በደቡብ ኮሪያ ንግድና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ኤጀንሲ የዕውቀት ሽግግር ፕሮግራም(Knowledge Sharing Program) ከፍተኛ አማካሪ ሚስተር ሲየንግል ቼል ሊ በበኩላቸው ጥናቱ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍ ልማት የኤክስፖርት ታሪፎችን የሀገር ውስጥ ታሪፍ ማሻሻያን እና የ መንግስትና የግል አጋርነት ግዢ ዋጋዎችን ወደ አንድ የድርድር ስርዓት ማቀናጀት እና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር የሚያስችል ነው ብለዋል።

ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ላይ የቆመና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ያረጋገጠ ተቋም ለመፍጠር በጥናቱ የተገኙ ውጤቶችና የተመላከቱ ምክረ ኃሳቦችን ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባ አንስተዋል።

የተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ደስታዓለም ኃይሉ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት ጠንካራ የፋይናንስ አቅም በመፍጠር የኃይል ልማት ዘርፉ ላይ ውጤት ለማስመዝገብ ጥናቱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

በጥናቱ የተመላከቱ ምክረ ሀሳቦችን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር አስማምቶ በመተግበር ውጤት ለማስመዝገብ ተቋሙ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

Scroll to Top