ስነ-ምግባርን በተላበሰ መንገድ ሥራን ማከናወን እንደሚገባ ተገለፀ

ስነ-ምግባርን በተላበሰ መንገድ ሥራን ማከናወን እንደሚገባ ተገለፀ

የሀገሪቱን ብሎም የተቋሙን ህግና መመሪያ ባከበረ እና ስነ-ምግባርን በተላበሰ መንገድ የዕለት ከዕለት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ተገለፀ።

የኮርፖሬት ፋይናንስ እና ሰው ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ ለፕሮጀክት ሠራተኞች እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና ላይ እንደገለፁት የስራ ላይ ስነ-ምግባር መርሆዎችን በውል በመገንዘብ እና ተግባራዊ በማድረግ የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ማሳደግ ይገባል።

ስነ-ምግባር የተቋሙን ተወዳዳሪነት የሚወስን ዋነኛ ምሰሶ በመሆኑ እያንዳንዱ ሰራተኛ ስራውን በታማኝነት፣ በቁርጠኝነትና በከፍተኛ የስራ ተነሳሽነት በማከናወን ለተቋሙ ስኬት የበኩሉን አሻራ ማሳረፍ እንዳለበት በአፅንኦት ገልፀዋል።

ስልጠናውን የሰጡት የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አጥናፌ በበኩላቸው ሰራተኞች የስራ ሰዓትን በማክበርና ሥራው የሚጠይቀውን ዲሲፕሊን በመላበስ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የስራ ዕቅድን በተያዘለት ጊዜ በጥራት አከናውኖ ማስረከብ ዋነኛው የስራ ላይ ስነ-ምግባር መገለጫ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ሥራዎች ሲከናወኑም ሆነ ሲመዘኑ ከዘር፣ ከኃይማኖት አድሎ እና ከጥቅም ትስስር በፀዳ መልኩ የስራ መርህን ብቻ መሠረት መደረግ እንዳለበት በአፅንኦት አሳስበዋል።

ስነ-ምግባራዊ አሠራርን ለህጋዊነት ማሟያ ብቻ ሳይሆን ህሊናን ሊያረካ በሚችል አኳኋን ማከናወን እንደሚገባ የገለፁት አቶ ደረጀ ይህም የሰራተኛውን በራስ መተማመን ከማጎልበት ባለፈ ለራሱና ለባልደረቦቹ ያለው ክብር ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የፕሮጀክት ሥራዎች በሚከናወኑበት ወቅት በየአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦችን ባህል እና እሴት ማክበር እንደሚገባና እንደተቋምም ሆነ በየስራ ክፍሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ ጣት ከመጠቋቆም ወጥቶ ለችግሩ እልባት ለመስጠት በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የተቋሙን ሚስጥርና አዕምሯዊ ንብረቶች በጥንቃቄ መጠበቅ እንዲሁም ትክክለኛ ሪፖርት ማቅረብ ግዴታ መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተሩ በስራ ከባቢ ውስጥ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ትንኮሳ እና ቁጣ የሚቀሰቅሱ ቀልዶች ከስነ-ምግባር ያፈነገጡ በመሆናቸው ሁሉም ሠራተኛ ከነዚህ ድርጊቶች መቆጠብ ይኖርበታል ብለዋል።

ለፕሮጀክት ሰራተኞች የተዘጋጀው ይህ ስልጠና በነገው ዕለትም ቀጥሎ እንደሚውል ታውቋል።

Scroll to Top