የተቋሙን ሁለንተናዊ ዕድገት ዘላቂ ለማድረግ ርዕይ ተኮር ሠራተኛ መገንባት እንደሚያስፈልግ በትራንስሚሽን ቢዝነስ የሰው ሀብት እና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተማም አፍደል ገለፁ።
በተቋሙ ርዕይ፣ ተልዕኮ እና የሥራ ባህል ላይ ያተኮረ ስልጠና የሰጡት ዳይሬክተሩ የተቋሙን ስትራቴጂካዊ ግብ ለማሳካት እያንዳንዱ ሠራተኛ በተሰማራበት የሥራ መስክ የተቋሙን መዳረሻ ባማከለ መንገድ ሥራውን ማከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።



አቶ ተማም እንደገለፁት የሠራተኞች ዋነኛ ተባር የተቋሙን ርዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴት በውል በመገንዘብ ሥራዎችን በተቀመጠላቸው የጥራት ደረጃ ማከናወን ላይ ነው። ይህም ተቋሙን ወደ ላቀ ደረጃ መድረስ ያስችለዋል ብለዋል።
የሠራተኛው ጤንነትና ደህንነት ሲጠበቅ የተቋሙ ምርታማነት በዚያው ልክ እንደሚያድግ የጠቀሱት አቶ ተማም ሠራተኞች ሁልጊዜም በሥራ ቦታ ላይ የተሟላ የሥራ ላይ ደህንነት አልባሳትን በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል።



እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የአንድ ተቋም ሁለንተናዊ ቁመና ትክክለኛ መሥመር ላይ መሆኑ የሚረጋገጠው ሠራተኛው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሥራዎችን በሕግና በመመሪያ ሲያከናውን ብቻ ነው።
በመሆኑም እያንዳንዱ ሠራተኛ የተቋሙን ክብርና ዝና በጠበቀ መልኩ ደንበኞችን ሊያስተናግድና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የተቋሙ አምባሳደር ሆኖ መሥራት እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።
በተጨማሪም የጋራ እሴቶች፣ መተማመን፣ መከባበር፣ ተጠያቂነት፣ የቡድን ሥራ እና ጠንካራ ተግባቦት የሰፈነበት የሥራ ከባቢ በመፍጠር ጠንካራ ተቋማዊ ባህል ሊዳብር እንደሚገባና በሥራ ወቅትም የተቋሙን ንብረቶች በጥንቃቄና በኃላፊነት ስሜት መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የስልጠናው ተሳታፊዎች በፕሮጀክቶች ላይ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያጋጥሟቸውን ዋና ዋና ተግዳሮቶች አንስተው ውይይት አድርገዋል።
ከተነሱት ችግሮች መካከል የግብዓት አቅርቦትና የውሎ አበል መዘግየት፣ የጅምላ ፍረጃ፣ የካሳ ክፍያ መስተጓጎል እና ምቹ ያልሆነ የሥራ ከባቢ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለተቋሙ የፕሮጀክት ሠራተኞች ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።



