ሁሉም ሠራተኛ የተቋሙ አምባሳደር ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

ሁሉም ሠራተኛ የተቋሙ አምባሳደር ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

በመላ ሀገሪቱ ለስራ የተሰማራ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኛ ባገኘው አጋጣሚ የተቋሙን ገፅታ በመገንባት እና ከደንበኞች ጋር ያለውን የስራ ግንኙነት በማሳደግ የተቋሙ አምባሳደር ሊሆን እንደሚገባ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ተወካይ ኃላፊ ግርማ ግዛቸው (ዶ/ር) አሳሰቡ።

ለፕሮጀክት ሠራተኞች በተሠጠው ሥልጠና ማጠቃለያ ላይ በመገኘት የቀጣይ የስራ መመሪያ የሰጡት ዶክተር ግርማ ተለዋዋጭ የሆነውን ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ እውቀትና ክህሎት በመታጠቅ ተቋሙን ይበልጥ ውጤታ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የስራ ሰዓትን ለታለመለት ዓላማ በማዋል ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ የአፈፃፀም ጉድለቶችን መቅረፍ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የተቋሙ ገቨርናንስ እና ኮምሊያንስ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዱጉማ ነዳ በበኩላቸው የተሰጡ ስልጠናዎችን ወደ ተግባር ማውረድ እንሚገባና ስልጠናው ያስገኘውን ለውጥ በቀጣይ የመገምገም ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የፕሮጀክት ግብአቶችን በወቅቱ አለማቅረብ፣የውሎ አበል መዘግየት እና የተሟላ የስራ ላይ ደህንነት አልባሳት እጥረት እንደሚስተዋል የገለፁት አቶ ድጉማ ችግሮቹን ለመፍታት በስራ ክፍልም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ተጠያቂነት እንደሚኖር አረጋግጠዋል።

ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም አንፃር ሁሉም የተቋሙ ሠራተኛ ተቋሙን ሊገነባ በሚችል አኳኋን ክፍተቶችን ማመላከት እንደሚገባው ገልፀው ነገር ግን የተቋሙንና የግለሰቦችን ገፅታ ከሚያጎድፉ ሐሰተኛ መረጃዎች መታቀብ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የሰው ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ መሠል ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁ ሲሆን ሆነ ብለው ስራን የሚያበላሹ እና ከስነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት የሚፈፅሙ ሠራተኞች ሲገኙ ግን በህብረት ስምምነት መሠረት አስተማሪ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

አቶ አታላይ አክለውም የስራ ሰዓትን ለታለመለት የፕሮጀክት ስራ ማዋል እና ስራን ከጥቅም ግጭት በነፃ መንገድ ማከናወን እንደሚገባም ነው ያስታወቁት።

የደንብ ልብስ እና የስራ ላይ ደህንነት አልባሳት የግዥ ችግሮችን እልባት ለመስጠት ግዢው በሪጅን፣በኃይል ማመንጫ እና በስራ ዘርፎች እንዲፈፀም መወሰኑን ተናግረዋል።

ለተቋሙ ሠራተኞች እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠና በቀጣይ ሳምንታት በተለያዩ ዙሮች መሰጠት እንደሚቀጥል ታውቋል።

Scroll to Top