በሥነ-ምግባር የታነጸና የበቃ ሠራተኛ በመፍጠር ሁሉን አቀፍ ተቋማዊ ለውጥ ለማስመዝገብ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
“የሠራተኞች ተሳትፎ ለተቋማዊ ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ለተቋሙ ሠራተኞች የሚሰጠው ሁለተኛ ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለት መሰጠት ተጀምሯል።

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዱጉማ ነዳ እንደገለጹት ተቋሙ ብቃት ያለው ሠራተኛ ለመፍጠር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በስፋት እየሰጠ ይገኛል።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚሰጠው ሥልጠና በሥነ-ምግባር የታነጸና ብቃት ያለው ሠራተኛ በመፍጠር ሁሉን አቀፍ ተቋማዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል።
ሥልጠናው ሠራተኛው ተቋሙ አሁን ያለበትን ደረጃ እና የወደፊት መዳረሻ ግቡን በውል ተገንዝቦ በአንድነት ለመንቀሳቀስ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ሠራተኛው የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም በተቋሙ ያሉ ሕግና መመሪያዎችን አውቆና አክብሮ ለመስራት ሥልጠናውን በአግባቡ መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል።



ለሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች የሚሰጠው ሥልጠና በሠራተኞች ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም በሥራ ቦታ ሥነ-ምግባር መርሆች ዙሪያ ትኩረት የሚያደርጉ ናቸው።
እስከ መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም ለዋናው መስሪያ ቤት ሁሉም ሠራተኞች እንዲሁም እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በሁሉም ሪጅኖችና ኃይል ማመንጫዎች ለሚገኙ ሠራተኞች ሥልጠናው እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ሥልጠናው በዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የፖሊሲ ፕሮሰስ እና ለውጥ ሥራ አመራር መምሪያ፥ በኮርፖሬት ፋይናንስ እና ሀብት
አስተዳደር ዘርፍ የሰው ኃብት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት እና ኢትዮ ፓወር አካዳሚ እንዲሁም በኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ የሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና መምሪያ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ነው።



