በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጠንካራ ተቋማዊ ባህል በመፍጠር ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማስመዝገብ ሠራተኛው ተግባርና ኃላፊነቱን ተገንዝቦ ለተቋሙ እሴቶች መኖር እንዳለበት ተገለጸ።
በሠራተኞች ተግባርና ኃላፊነት ዙሪያ ሥልጠና የሰጡት በተቋሙ ትራንስሚሽን ቢዝነስ የሰው ሀብት እና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተማም አፍደል እንደገለጹት በተቋሙ የማያቋርጥ ለውጥ ለማስመዝገብ የሠው ኃይሉንና ሀብቱን አቀናጅቶ መጠቀም ይገባል።

በሥልጠናው በተቋሙ ስትራቴጂካዊ መነሻዎች፣ በሠራተኞች ተግባርና ኃላፊነት፣ በጠንካራ ተቋማዊ ባህል፣ በሥራ ላይ ደህንነት፣ በኦፕሬሽንና የቴክኒክ ግዴታዎች፣ በሙያዊ ሥነ-ምግባርና ታማኝነት፣ በደንበኞችና ባለድርሻ አካላት አያያዝ፣ በአፈጻጸም እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል ዙሪያ ገለጻ ሰጥተዋል።
ሁሉም ሠራተኛ ሚናውን ተገንዝቦ ተቋማዊ እሴትን በማክበር፣ ቁልፍ የአፈፃፀም መለኪያዎችን በመጠቀም፣ መልካም ተሞክሮዎችን ቀምሮ በማስፋት እንዲሁም ብክነትን በማስወገድ ውጤት ለማስመዝገብ መረባረብ እንዳለበት ገልጸዋል።


ተቋም ዘላቂና ውጤታማ የሚያደርገው ሁሉም ተደምሮ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሲወጣ በመሆኑ የእውቀት ሽግግርን ማዕከል አድርጎ በኃላፊነት እንዲሰራ አብራርተዋል።
ጎታች አስተሳሰቦችን በመታገል፣ ሚናን ለይቶ በመስራት እና ሥራን በአግባቡ በመለካት እንዲሁም ለመማር ዝግጁ በመሆን ጥራትና የሥራ ላይ ደህንነትን ባረጋገጠ አግባብ መስራት የሁሉም ሠራተኛ ሚና ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


እንደ አቶ ተማም ገለፃ ሠራተኛው የተቋሙን ገፅታ ከሚያጎድፉ ጉዳዮች በመራቅ እንዲሁም ሕግ፣ ደንብ እና የሥራ ሥነ-ምግባርን አክብሮ የመሥራት ኃላፊነት አለበት።
መረጃን አለማጋራት፣ ፍርሃትን መሠረት ያደረገ የሥራ ከባቢ፣ ችግሮችን መደበቅ፣ ለለውጥ የሚደረግን ውይይትን መቃወም፣ የግል ጥቅምን ማስቀደም፣ ስህተትን ወይም ድክመትን በሌሎች ማሳበብ እና ክፍፍል መፍጠር የደካማ የሥራ ባህል መገለጫዎች መሆናቸውም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት፣ በቡድንና በትብብር የመሥራት፣ የባለቤትነት ስሜትና ድርጅትን የመውደድ፣ ራስን እያሳደጉ የመሄድ፣ በሙያቸው የላቁ ሠራተኞች መኖር በተቋሙ በበጎ የሚነሱ የሥራ ባህሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።


ለጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ከመስጠት፣ ከቢዝነስ ግንዛቤ፣ የጋራ ርዕይና ግብ ይዞ ከመንቀሳቀስ፣ የሥራ ላይ ደህንነት መርሆችን ከመከተል፣ ለለውጥ ዝግጁ ከመሆን፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ከግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከማጋራት እና ከዕውቀት ሽግግር ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም ጠንካራና የዳበረ ተቋማዊ ባህል ለመገንባት ሠራተኛው የጋራ እሴትና ግልጽ ዓለማ በመያዝ ሚናውን በባለቤትነት ስሜት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ከአመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ ከተቋሙ ርዕይ፣ ከሥልጠናው ተተግባሪነት እና ሌሎች ተያያዥ ተቋማዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡


