በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ 3 ሪጅን በሰበታ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ ወደ ፓወር ትራንስፎርመሩ ሳይሸጋገር አደጋውን ለተቆጣጠሩ የጣቢያው ሠራተኞች እውቅና ሰጥቷል፡፡
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ እስማኤል ሙዘይን በእውቅና ሥነ- ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ሪጅኑ በማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላክል ባለፉት ሁለት ዓመታት ለሠራተኞች ተከታታይ የእሳት አደጋ መከላከያ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

የሰበታ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ሠራተኞች ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ሦስት ሠዓት አካባቢ በጣቢያው እሳት ሲነሳ አደጋውን ለመቆጣጠር የወሰዱት ስልጠና አስተዋጽኦ ማድረጉንና በቀጣይ የእሳት አደጋ መከላከያና የመጀመሪያ እርዳት ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግውረዋል፡፡
ትራንስፎርመሩ ጉዳት ቢደርስበት ኖሮ ተቋሙ ለትራንስፎርመር ቅየራ የሚያወጣውን እና ኃይል ተቋርጦ በሚቆይበት ጊዜ ከኃይል ሽያጭ ከሚያጣው ኪሳራ ባለፈ የኃይል መቋረጥ በማስከተል በአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ያሳደርስ እንደነበር አቶ እስማኤል አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም የጣቢያው ሠራተኞች ቅድሚያ ንብረቱን ከጉዳት መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ አደጋው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በመከላከል ተቋሙን ከኪሳራ መታደጋቸውን ነው ያነሱት፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው ሠራተኞች አደጋውን ለመቆጣጠር ላከናወኑት ሥራ ሪጅኑ እውቅና መስጠቱ ሠራተኞችን ለተሻለ ውጤት ከማበረታታት ባለፈ ሠራተኞች ያከናወኑት ሥራ በሌሎች የጣቢያ ሠራተኞች በምሳሌነት የሚወሰድ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡


እንደ አቶ እስማኤል ገለፃ ከመደበኛ ሥራዎች በተጨማሪ ችግሮች ሲያጋጥሙ በአካባቢው ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ ክፍሎች ጋር በጋራ በመሆን መፍትሔ እንደሚሰጥና አገልግሎቱ እስከአሁን ላደረገው ድጋፍም ሪጅኑ የምስክር ወረቀት እውቅና አበርክቷል፡፡
በሪጅኑ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ገብሬ በበኩላቸው በ15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመር ችግር ምክንያት በጣቢያው በአርዚንግ ትራንስፎርመሩ ላይ የእሳት አደጋ መነሳቱን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም የእሳት አደጋው ወደ ፓወር ትራንስፎርመሩ ሳይሸጋገር በጣቢያዉ ሠራተኞች አማካይነት በቁጥጥር መዋሉን አንስተዋል፡፡
ሠራተኞችን ለተቋሙ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሪጅኑ እውቅና መስጠቱ ሠራተኞችን ለተሻላ ሥራ የሚያነሳሳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ እውቅና የተሠጣቸው የጣቢያው ሠራተኞች እንደገለጹት ችግሩን በወቅቱ መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ አደጋው በቀላሉ ወደ ትራንስፎርመሮች በመሸጋገርና በጣቢያው ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በኃይል አቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድር ነበር፡፡
አደጋውን ሁሉም የጣቢያው ሠራተኛ በመቀናጀትና የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን በመጠቀም ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ስለመቻሉም አንስተዋል፡፡
በሪጅኑ የተሰጣቸው እውቅና ለተሻለ ሥራ እንዲዘጋጁ ግብዓት እንደሚሆናቸው የገለፁት ሠራተኞቹ በቀጣይ የጣቢያውን ደህንነት ለማረጋገጥ የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የምዕራብ አዲስ አበባ ሪጅን የዲስትሪቢውሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ኃላፊ አቶ እስመሄር እሸቴ እና የዲስትሪቢውሽን መቆጣጠሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ግርማ በበኩላቸው ለደንበኞች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ከሪጅኑ ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡


በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከላዊ ሪጅን የተሠጠው እውቅና የትብብር ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሚያግዝም አንስተዋል፡፡
በቀጣይ ከወጭ መስመር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ጨምሮ ለኃይል መቋረጥና ለተለያዩ አደጋዎች ምክንያት የሆኑ የተለያዩ ችግሮችን በጋራ በመሆን ለመፍታት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
በዕለቱ በማከፋፈያ ጣቢያው ላይ ላጋጠመው ችግር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ የተከናወኑ ሥራዎችና በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚገቡ የቅድመ መከላከያ ጉዳዮች በተመለከተ በሪጅኑ የፕሮቴክሽን መሐንዲስ የሆኑት በአቶ መላኩ ገብሬ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡





