የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የፍተሻና የሙከራ ሥራ በስኬት መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ጌቱ ያደታ እንዳስታወቁት ማከፋፈያ ጣቢያው ከሦስት አቅጣጫ በአራት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲገናኝ በማድረግ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ጣቢያው ከቆቃ፣ ከመልካዋከና እና ከበቆጂ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጋር ለማገናኘት የሁለት የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎችና የሽቦ ዝርጋታ ሥራ በተቋሙ የራስ ኃይል መምሪያ መከናወኑንም ነው አቶ ጌቱ የጠቆሙት።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የኮሙዩኒኬሽን፣ የስካዳ እና የመቆጣጠሪያ ሥርዓቶች በተቋሙ ባለሙያዎች ተሰርተው ትራንስፎርመሮቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮችና 4 ገቢ መስመሮች እንዳሉትም ነው የጠቀሱት።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በቀጣይ 40 በመቶ የቅድመ ፍተሻ ሥራ የተከናወነላቸውን የንፋስ ተርባይኖች ከኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ጋር በማገናኘት ኃይል እንዲያመነጩ ይደረጋል።
በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በየሳምንቱ 10 ሜጋ ዋት በድምሩ 80 ሜጋ ዋት ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ነው አቶ ጌቱ የገለፁት።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ እንደ ሀገር ከንፋስ የሚመነጨውን ኃይል ከ404 ሜጋ ዋት ወደ 504 ሜጋ ዋት ከፍ በማድረግ የኃይል ስብጥሩን ለማሳደግና አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ያስችላል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



