የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምስራቅ 2 ሪጂን ሥር የሚገኘውን የሠመራ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ አስታወቁ።

ኃላፊው አቶ እንድሪስ አህመድ እንደገለፁት የጣቢያውን የኦፕሬሽን አቅም ለማሳደግ በባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች የዘመናዊ መቆጣጠሪያ ብሬከር ቅየራ ሥራ እየተከናወነ ነው።

በማከፋፈያ ጣቢያው ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥ  የቆየውን ኤር ኢንሱሌትድ ስዊች ጊር ወደ  ጋዝ ኢንሱሌትድ ስዊችጊር ብሬከር  የመቀየር ሥራ መሰራቱ የጣቢያውን የኦፕሬሽን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የብሬከር ቅየራው አሁን ላይ 70 በመቶ መድረሱንና ሲጠናቀቅ የጣቢያውን ኃይል የማቅረብ አቅም አስተማማኝና የተቀላጠፈ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።

የሪጂኑ ጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ሙሀመድ አብዱ በበኩላቸው የሠመራ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የዘመናዊ መቆጣጠሪያ ብሬከር ቅየራ ለሠመራ፣ ለሎጊያ፣ ለሚሌ፣ ለአሳይታ፣ ለዱብቲ ከተሞችና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተማማኝ ኃይል ማቅረብ ያስችላል ብለዋል።

የሰመራ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከኮምቦልቻ በ 230 ኪሎ ቮልት የተቀበለውን ኃይል ወደ አፍዴራና ዲቾቶ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በማስተላለፍ ከ80 በመቶ በላይ የሆነውን የአፋር ክልል ተደራሽ ያደርጋል።

አንድ ገቢ መስመርና ሁለት ወጪ መስመሮች ያሉት የሰመራ ማከፋፈያ ጣቢያ በ2003 ዓ.ም  ተገንብቶ ለክልሉ በዋነኛነት ኃይል በማቅረብ እያገለገለ ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top