በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት መከላከል ይገባል

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት መከላከል ይገባል

በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸመው ተደጋጋሚ ስርቆት ለመከላከል የሚያስችል ውይይት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ከተማ ተካሄደ።

በውይይቱ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች እና የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

መስመሩ የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ዕቃዎች የሚጓጓዙበት መሆኑን በውል መረዳት እንደሚያስፈልግ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል።

በባቡር መስመሩ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በሚፈጸም ተደጋጋሚ ስርቆት የተነሳ የባቡር መስመሩን ሙሉ አቅም ለመጠቀም እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም ገቢ እና ወጪ ዕቃዎች እንዲዘገዩ በማድረግ በዓለምአቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን በመቀነስ እና የዋጋ ንረትን በማስከተል በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት፣ ማህበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በባቡር መስመሩ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀመውን ስርቆት ለመከላከል ከመንግሥት ጎን በመሆን የማጋለጥ ስራ እየሰሩ መሆኑን እና ይሄን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገቢያ የባቡር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ላይ በአስር ቀናት ውስጥ ብቻ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ እና 25 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ለስርቆት መዳረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top