ማከፋፈያ ጣቢያው አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ ነው

ማከፋፈያ ጣቢያው አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰበታ ሁለት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የጣቢያው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አየልኝ እንደገለጹት በባለ 400 ኪሎ ቮልት በሀገሪቱ የመጀመሪያው የነበረው ማከፋፈያ ጣቢያው በ2002 ዓ.ም ወደ ሥራ ሲጀምር በዋናነት የግልገል ጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ኃይል ተቀብሎ ለማስተላለፍ ነው።

ጣቢያው ከግልገል ጊቤ 2 በገላን ማከፋፈያ ጣቢያ በኩል እንዲሁም ከጊቤ 3 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እና ከሆለታ ማከፋፈያ ጣቢያ በ 400 ኪሎ ቮልት አራት ገቢ መስመሮች ሲኖሩት ካራ ቆሬ አካባቢ ለሚገኘው ሰበታ አንድ ማከፋፈያ ጣቢያ  እንዲሁም ለኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር በ230 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር ኃይል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በማከፋፈያ ጣቢያው ዙሪያ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ለፋብሪካዎች በ33 ኪሎ ቮልት ኃይል የሚሰጥ ሲሆን ከ34 በላይ ወጪ መስመሮች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 250 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት አውቶ ትራንስፎርመሮች እንዳሉት የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ በሦስት መስመር ወደ 60 ሜጋ ዋት አካባቢ ኃይል ለዳታ ማይኒንግ ድርጅት እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡

የሰበታ ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ በ 400 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመነጨውን ኃይል ከሆለታ ማከፋፈያ ጣቢያ ተቀብሎ ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እያስገባ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በቀጣይም የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለመጨመር አንድ ተጨማሪ አውቶ ትራንስፎርመር እና ለአካባቢው ማሕበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ፓወር ትራንስፎርመር ከውጪ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top