በማመንጫ ጣቢያው የዕቃ ግምጃ ቤት የካይዘን አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል

በማመንጫ ጣቢያው የዕቃ ግምጃ ቤት የካይዘን አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጊቤ ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የዕቃ ግምጃ ቤቶች የካይዘን አሰራር ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን ጣቢያው አስታወቀ።

የጣቢያው የጥገና ባለሙያ አቶ እሸቱ አበራ እንደተናገሩት የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎችን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ የካይዘን የአሰራር ሥርዓትን በዕቃ ግምጃ ቤቶች ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል።

የካይዘን የአሰራር ሥርዓት ከመተግበሩ በፊት የዕቃ ግምጃ ቤቶቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ዕቃዎቹም በተለያዩ ቦታ በዘፈቀደ የተቀመጡ እንደነበረ አስታውሰዋል።

በዚህም ዕቃዎቹ በሙቀትና በተለያዬ ምክንያቶች በአጭር ጊዜ ከመበላሸታቸውም በተጨማሪ ለሥራ ሲፈለጉ በቀላሉ የማይገኙ በመሆኑ ውጤታማ የኦፕሬሽን እና የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን አዳጋች ነበር ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በካይዘን የአሰራር ሥርዓት ግንዛቤ ያላቸው ባለሙያዎች ተመድበው ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በጣቢያው በሚገኙ ሦስት የዕቃ ግምጃ ቤቶች ላይ የሚሰሩና የሚወገዱ የመለዋወጫ ዕቃዎችና መሣሪያዎችን በመለየት በዓይነታቸውና በአገልግሎት ዘመናቸው መሰረት ከሦስት ወር በላይ ጊዜ በመውሰድ የማደራጀት ሥራ ተሰርቷል።

ይህም ጣቢያው ያሉትንና የሌሉትን የመለዋወጫ ዕቃዎች ለይቶ እንዲያውቅ በማስቻሉ ቀደም ሲል ዕቃዎቹን ለመፈለግ ይወስድ የነበረውን ጊዜና በብልሽት ምክንያት ያጋጥም የነበረውን አላስፈላጊ ወጭ ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።

የጣቢያው የዕቃ ግምጃ ቤት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ  ማርታ ጉንቴ በበኩላቸው ከሦስት ወር በላይ ጊዜ በመውሰድ የተደራጁት ዕቃዎች ዓይነትና ዝርዝር መረጃዎች መለያ ተሰጥቷቸው ተመዝግበው መቀመጣቸውን ገልጸዋል።

ይህም በግምጃ ቤቱ ውስጥ ያሉ ዕቃዎችን ለማወቅ፣ ያለቁ ዕቃዎችን ለማሟላት እና የሚገቡ ዕቃዎችን በዓይነታቸው አደራጅቶ በማስቀመጥ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከአራት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ጋር የካይዘን ትግበራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top