ሪጅኖች ተቋማዊ ለውጡን በሚያሳካ መልኩ የኦፕሬሽን ሥራዎችን ሊያከናውኑ እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ አሳሰበ።
ዘርፉ የሪጅኖችን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ ሰጥቷል።
በተቋሙ የትራንስሚሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዷለም ሲዓ እንደተናገሩት ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንዲያስችለው ተቋማዊ ለውጥ እየተገበረ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ውጤታማ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያልተከናወኑ ተግባራትንና በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ለማከናወን የታቀዱ ሥራዎችን በማካተት የመቶ ቀን ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አሳስበዋል።
ዕቅዱን በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የጋራ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገባ ያሳሰቡት አቶ አንዷለም ዕቅዱ ሪጅኖች ያሉበትን የአፈጻጸም ደረጃ የለየ፣ ችግሮችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ፣ የሥራ ቅደም ተከተልንና ባለቤት የለየ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በመቶ ቀን ዕቅዱ በተለያዩ ምክንያቶች የግሪድ መሳሳት ባጋጠሙ ቦታዎች ላይ አስፈላጊ ሥራዎችን በመስራት ግሪዱን ወደነበረበት አቅምና አቋም ለመመለስ ትኩረት እንዲሰጥ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የኦፕሬሽን ሥራዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም ሪጅኖች ከሠራተኞች ጋር መግባባት መፍጠርና መፍጠንን ማዕከል በማድረግ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የማዕከላዊ አንድ ሪጅን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ገዛኸኝ እንደገለጹት የግምገማ መድረኩ ተቋማዊ ለውጡን ሪጅኖች በምን መልኩ ማስኬድ አለባቸው በሚለው ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ የፈጠረ ነው።
መድረኩ በሪጅኖች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ በቀጣይ ለመፍታት እና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ለውጥ ለማስመዝገብ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰሜን ምስራቅ ሁለት ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ሀሰን ሙሐመድ በበኩላቸው የግምገማ መድረኩ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበት እንዲሁም የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር በቀጣይ በምን መልኩ መሰራት አለበት በሚለው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ያገኘንበት ነው ብለዋል።
እንደሪጅን ያሉ ችግሮችን እና መልካም አጋጣሚዎችን በመለየት የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን አስቀምጦ ስጋቶችን በቀነሰ መልኩ ለተቋማዊ ለውጡ ስኬት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



