ሪጅኖች የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማቀላጠፍ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር መስራት አለባቸው

ሪጅኖች የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማቀላጠፍ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር መስራት አለባቸው

የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽን ሥራ በማቀላጠፍ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር መስራት እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሳሰቡ።

የትራንስሚሽን ቢዝነስ 13ቱም የሪጅን ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡

ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ አንዷለም ሲዓ እንደተናገሩት ግምገማው የሪጅኖች የኦፕሬሽን ሥራ ያለበትትን ደረጃ ለማወቅ፣ እርስ በእርስ ለመማማር፣ ከኦዲት ጋር ተያይዞ የተሰሩ ማሻሻያዎችን ለማየት እና አመራሩ በአፈፃፀሙ ላይ የጋራ ግንዛቤ ኖሮት ሥራዎችን እንዲሰራ ዕድል ለመፍጠር ነው፡፡

ዘርፉ እንደ አዲስ ከተዋቀረ በኋላ ቀደም ሲል በችግር መልክ ሲነሱ የቆዩና መፍትሄ ያላገኙ ጉዳዮችን በመለየት በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሁም የኦፕሬሽን አሰራሮችን ለማዘመንና ለማሻሻል ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

አቶ አንዷለም አክለውም ሪጅኖች የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማቀላጠፍ እንዲሁም ከአካባቢ መስተዳድር አካላትና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲስትሪክት ኃላፊዎች ጋር በመቀናጀት የኃይል ተደራሽነቱን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የዘርፉ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን የዕቅድና ክትትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታገል ደገፉ ቀርቧል፡፡

የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የቅድመ መከላከል፣ የትንበያ፣ የፍተሻ ጥገና ሥራዎች በማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፍያ ጣቢያዎች ላይ መከናወናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በሰመራና በአዲጋላ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በጭነት ልዩነት ወቅት ቮልቴጅን ለመቀጣጠር የሚረዳ መሣሪያ (shunt reactor) በመትከልና ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት የአፋር ክልልና የጅቡቲን የኤክስፖርት ኮሪደር እንዲሁም የባቡር ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን አስተማማኝና ያልተቆራረጠ ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡

የዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ብሬከሮች ተከላ እንዲሁም በስርቆት ምክንያት የሚወድቁ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን መልሶ የመገንባት ሥራዎች በራስ አቅም በማከናወን ወጭና ጊዜ መቆጠብ መቻሉም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የመለዋወጫ እቃዎች ተመዝግበው መቀመጣቸው፣ በአስራ ስድስት ማከፋፈያ ጣቢዎች ላይ ላይ የፕሮቴክሽን ማሻሻያ ሥራዎችን በመስራት የብሔራዊ የኃይል ቋቱን ደህንነት ከፍ በማድረግ አላስፈላጊ የኃይል መቆራረጦችን መቀነስ ተችሏል፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት መጨመር፣ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተለያዩ መስመሮች ለረዥም ጊዜ ተቋርጠዉ መቆየት፣ የከፍተኛ ኃይል ትራንስፎርመር እጥረት እና በማሰራጫ መስመሮች ላይ በሚያጋጥም አደጋ ምክንያት የሚወጡ መስመሮች እና ትራንስፎርመሮች መጨመር በዘጠኝ ወራት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ አበባው ያለው በበኩላቸው ግምገማውን ማድረግ ያስፈለገበት ዋና ምክንት በተቋሙ እየተከናወኑ ካሉ ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎች ጋር ተያይዞ በኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ መዘናጋት እንዳይኖር ያለበትን ደረጃ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል፡፡

የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት በ36 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማሻሻያና የአቅም ማሳደግ ሥራዎችን በራስ አቅም እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኃይል ያላገኙ አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ኃይል ባገኙ አካባቢዎች አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ የዘርፉን አፈፃፀም ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበባው የኦፕሬሽን ሥራዎችን ለማዘመን እና አሰራሮችን ለማሻሻል እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ግምገማው በነገው ዕለትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top