የጣቢያው ሁለተኛ የግንባታ ምዕራፍ እየተከናወነ ነው

የጣቢያው ሁለተኛ የግንባታ ምዕራፍ እየተከናወነ ነው

የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሁለተኛው  የግንባታ ምዕራፍ  በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪ ተወካይ ሪዚደንት መሀንዲስ አስታወቁ::

ተወካዩ አቶ ሰለሞን ክንፈ እንደገለፁት የጣቢያው ግንባታ በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ 32 የንፋስ ተርባይኖችን በመትከል 80 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ባለው በሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ደግሞ የ16 ተርባይኖች ተከላ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ይህም ጣቢያው ተጨማሪ 40 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ የሚያስችለው ሲሆን አጠቃላይ የማመንጨት አቅሙን 120 ሜጋ ዋት በማድረስ ሀገሪቱ በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የተርባይኖቹ ተከላ ሥራ ከዚህ ቀደም በፋይናንስ አቅርቦት ምክንያት መዘግየቱን ያስታወሱት ተወካዩ በአሁኑ ወቅት ግን ተቋሙ በራሱ የፋይናንስ ወጪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ወስኖ ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል።

በዚህም መሠረት የስምንት ንፋስ ተርባይኖች ሙሉ ዕቃዎች እና የአራት ተርባይኖች ተሸካሚ ምሰሶዎች ወደ ሳይት ደርሰዋል። የሌሎች አራት ተርባይኖችና ቀሪ ተያያዥ ዕቃዎች የምርት ሂደት ተጠናቆ ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዙ ይገኛሉ።

ከዚህ ቀደም ተርባይኖቹን ለመትከል የሚያስችለው የመሠረት ቁፋሮና የኮንክሪት ሙሌት ሥራና የሦስት ተርባይኖች ተከላ ተጠናቋል። በተጨማሪም የሰባት ተርባይኖች ጀነሬተር ተከላ ሥራን በማጠናቀቅ የአራት ተርባይኖች የንፋስ መቅዘፊያ ክንፎችን መሬት ላይ የመገጣጠም ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በቀጣይም የተከላ ሥራቸው የተጠናቀቁትን ተርባይኖች ከጣቢያው ማከፋፈያ (Switchyard) ጋር ለማገናኘት የሚያስችሉ የኬብል መሳብ ተግባራትን በማከናወን የሙከራና የፍተሻ ሥራዎች እንደሚጀመሩ አቶ ሰለሞን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የአካባቢው የንፋስ ሁኔታ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ተወካዩ አሁን ባለው የግንባታ ሂደት እየታየ ያለው አፈፃፀም በታቀደው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከተርባይን ተከላው ሥራ ጎን ለጎንም በጣቢያው ውስጥ የሚገኙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችሉ የዲዛይን ሥራዎች በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top