ተቋሙን ከተለያዩ የሕግና የፋይናንስ ስጋቶች ለመከላከል በትኩረት መስራት ይገባል

ተቋሙን ከተለያዩ የሕግና የፋይናንስ ስጋቶች ለመከላከል በትኩረት መስራት ይገባል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ገቨርናንስ እና ኮምፕሊያንስ ሥራ አስፈፃሚ ተቋሙን ከተለያዩ የሕግና የፋይናንስ ስጋቶች ለመከላከል በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳሰቡ።

ይህ መልዕክት የተላለፈው ተቋሙ ለሕግ ባለሙያዎቹ በሕግና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ  ሥልጠና እንዲሰጥለት ለፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በተዘጋጀው የሥልጠና ማጠናቀቂያ መርሃ-ግብር ላይ ነው።

የኮርፖሬት ገቨርናንስ እና ኮምፕሊያንስ ሥራ አስፈፃሚው አቶ ዱጉማ ነዳ ባስተላለፉት መልዕክት ሥልጠናው የሕግ ባለሙያዎቹ ከተቋሙ ነባራዊ ሁኔታና የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ጋር የተጣጣመ የላቀ የሕግ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በእጅጉ ያግዛል።

ተቋሙ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰራ በመሆኑ የሚደረጉ ትልልቅ የውል ሥምምነቶች በተቋሙ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ውጤቶች በጥልቀት መመርመርና መከታተል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ይህ ሥልጠና በተለይ በቅርቡ ተቋሙን የተቀላቀሉ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በቅርብ የተመረቁና ሰፊ የሥራ ልምድ የሌላቸውን ጀማሪ የሕግ ባለሙያዎች ታሳቢ ያደረገ ነው።

አቶ ዱጉማ አክለውም ይህም ባለሙያዎቹ በሥራ ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከሀገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ ጋር በማስተሳሰር መፍትሔ እንዲያበጁ ለማስቻል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ሰልጣኞች በሥልጠናው ወቅት ያገኟቸውን ዕውቀቶችና ልምዶች ወደ ተግባር በመቀየር በተቋሙ ውስጥ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶችን ለመሙላትና የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዘካሪያስ ኤርኮላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በፍትሕ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የሕግ ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግና ተቋማዊ አሠራርን ለማሻሻል ዘርፈ-ብዙ የሥልጠናና የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ በሀገሪቱ የሚወጡ የተለያዩ ሕጎችና ደንቦች ለሕግ አስከባሪዎችና ለዳኞች በቀላሉ ተደራሽና ሥልታዊ በሆነ መንገድ የተተነተኑ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ እንደ ዋና የሕግ መረጃ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በፍትሕ ዘርፉ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አካላት እርስ በርስ እንዲናበቡ አንዱ ያከናወነው ማሻሻያ ለሌላው ተቋም ግንባታ ግብዓት እንዲሆንና የተቀናጀ አሠራር እንዲሰፍን የሪፎርም ሥራዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ይህ ሥልጠና በኃይል ልማት ዘርፍ ውስጥ እየሰሩ ለሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ከአሰሪና ሠራተኛ፣ ከግዥ፣ ከውል አዘገጃጀትና አስተዳደር እንዲሁም ከንግድ ሕግ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ክርክሮችንና የሕግ ጥያቄዎችን በብቃት ለመፍታት የሚያስችል አቅም ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

በተቋሙ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም በቀለ በበኩላቸው ሥልጠናው ወደ ተቋሙ የሚመጡ ማናቸውንም የሕግ ጥያቄዎችና ክርክሮች በአግባቡ ለመያዝ እና ጉዳቶች እንዳይገጥሙ አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችል ገልፀዋል።

ይህም የተቋሙን መብትና ጥቅም በበለጠ ሁኔታ ለማስጠበቅና የላቀ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ከማገዙም ባሻገር ባለሙያዎቹ ከዳኞችና ከአቃቤ ሕግ አንፃር ያሉ የአሰራር ሥርዓቶችንና አተገባበሮችን በሚገባ እንዲረዱ ያደርጋቸዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ሥልጠናው በአሰሪና ሠራተኛ በፍትሐ-ብሔር ሥነ-ሥርዓት እና በአማራጭ የሙግት መፍቻ እንዲሁም በማስረጃ፣ በታክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ እና በግዥ ሕጎች ላይ ያተኮረ ነበር።

በፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ለ20 ቀናት ሲሰጥ የቆየው ይህ ሥልጠና ሲጠናቀቅም ለሕግ ባለሙያዎቹ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

Scroll to Top