የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን የሥራ ቅልጥፍና ለማምጣት የሚያስችል አውደ ጥናት ትናንት አካሄደ፡፡
አውደ ጥናቱ በዋናነት በጣቢያው ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት የጣቢያውን ኃይል የማምረት ዘላቂነት እና አስተማማኝነት ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡
በተቋሙ የኢትዮ-ፓወር አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ወንዶሰን ካሳ አውደ ጥናቱን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ማመንጫ ጣቢያው ኃይል ከማምረት ባሻገር ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የብክለት እና የእይታ ጉድለቶችን በመቅረፍ ከተማዋን ለማስዋብ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
ጣቢያው ለህብረተሰቡ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጨባጭ ጥቅሞችን እየሰጠ የከተማ አካባቢ ችግሮችን እንዴት እንደሚፈታ ለአፍሪካ ጭምር ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።
በዕለቱም የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ኃይል ከማመንጨት ጎን ለጎን የመዲናዋን ቆሻሻ ተቀብሎ ወደ ጥቅም በመቀየር ፅዱ፣አረንጓዴ እና ለጤና ተስማሚ ከተማ ለማድረግ ስለሚኖረው ፋይዳ እና እያጋጠሙት ስላሉ ተግዳሮቶች የተመለከተ አውደ ጥናት ቀርቧል፡፡
በጥናቱ ከቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ለከተማ ቆሻሻ አያያዝ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ያለውን ጥቅም ከአለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር በማነፃፀር በሠፊው ተዳሷል፡፡
በአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ማስረሻ አስናቀው ባቀረቡት ጥናት ላይ እንዳብረሩት ቆሻሻን ወደ ጥቅም መቀየር የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ቁልፍ ቴክኖሎጂ ነው።
ይሁን እንጅ በከተማዋ የሚሰበሰበው ቆሻሻ ከፍተኛ እርጥበት ያለው፣ለመቀጣጠል የማይመች እና የተቀላቀለ በመሆኑ በጣቢያው ኃይል የማምረት ሂደት ላይ ችግር እንደሚፈጥር በጥናቱ አመላክተዋል፡፡
በቆሻሻ አሰባሰብ ፣አወጋገድ እና አጠቃቀም ዙሪያ ደጋፊ የህግ ማዕቀፍ አለመዘጋጀቱ እንዲሁም የግንዛቤ እጥረት እና የተሳሳቱ አመለካከቶች መኖራቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።
በአውደ ጥናቱ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት የአጭር፣የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን አቅዶ መስራት እንደሚገባ ባለድርሻ አካላቱ በውይይታቸው አንስተዋል፡፡
ማመንጫውን የዋጀ የቆሻሻ አሰባሰብ ሥርዓት በመዘርጋት፣ስለቆሻሻ አስተዳደር የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት የቆሻሻ ሃብትን ወደ ጥቅም ለመቀየር በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተወያዮቹ አስገንዝበዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ፣ ከውሃና ኢነርጅ ሚንስቴር፣ ከአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር እና ከሌሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ታድመዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”