በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትብብር እና ተሳትፎ የተገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ የማንሰራራት ዘመን ማሳያ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለፁ፡፡
ተቋሙ በሰው ኃይል ልማት፣ በፋይናንስ፣ በኃይል ማመንጨት፣ በማስተላለፊያ፣ በማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽን፣ ግንባታና የጥገና እንዲሁም የሪፎርም ሥራዎች አፈፃፀምን ገምግሟል።
የበጀት ዓመቱን አፈፃፀም ያቀረቡት በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዱዓለም ሲዓ እንደገለፁት ተቋም የሚቀየረው የሠራተኛውን አቅም በማሳደግ በሚሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን የተናገሩት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው በሁሉም ዘርፍ የነበረው አፈፃፀም እንዲሁም የኦፕሬሽን ሥራዎች እና የኃይል ሽያጭ የተሻለ እንደነበር ገልፀዋል።
እንደ ኢንጂነር አንዱዓለም ገለፃ ለዓመታት ሳይከለስ የቆየውን የኤሌክትሪክ ታሪፍ የማሻሻል ሥራን በማከናወን ተቋሙ የተሻለ ገቢ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡
በበጀት ዓመቱ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከጅማሬ አንስቶ፣ በትግበራ ሂደት እና በማጠቃለያ ወቅት ያላቸውን አፈፃፀም እንዲሁም አጠቃላይ መረጃዎቻቸውን መመዝገብ የሚያስችል መተግበሪያ ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ መዋሉን ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አንድ አጠቃላይ የኃይል መቋረጥ በግሪድ ሥርዓቱ ላይ ማጋጠሙ፣ በግዥ የአሰራር ሥርዓቶች የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ክፍተት መታየቱ፣ የመቆጣጠሪያ ሥርዓቶችን የማዘመንና ወጥነት ያለው ሥራ አለመሰራቱ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮችን በተሟላ ሁኔታ መተግበር አለመቻሉ በበጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶች መሆናቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡
በውይይቱ ላይ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የታየውን ትብብር እና በጋራ የመልማት ቁርጠኝነት በሌሎች ፕሮጀክቶች መድገም እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማሳያ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል።
የህብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማሟላት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈፃሚው በማረጋገጥ የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሙስናን በመዋጋት የተቋሙን መልካም ሥምና ዝና በማስጠበቅ ረገድ ሁሉም የሥራ አመራር እና ሠራተኛ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሚመለከታቸው የዘርፍ ሥራ አስፈፃሚዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”