ማመንጫ ጣቢያ የወረዳውን የኢንቨስትመንትና የማህበራዊ ኑሮ ገጽታ ለውጧል

ማመንጫ ጣቢያ የወረዳውን የኢንቨስትመንትና የማህበራዊ ኑሮ ገጽታ ለውጧል

የመልካ ዋከና ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአዳባ ወረዳ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ከማሳደጉም በላይ የበርካታ ሺህ ነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ በእጅጉ ማሻሻሉን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።

የአዳባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱከሪም ከድር እንደገለፁት የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በወረዳው ውስጥ መገኘት አካባቢውን ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ በማድረግ የልማት ዕድገቱን አፋጥኖታል። በዚህም ምክንያት ከወረዳው 22 የገጠር ቀበሌዎች መካከል 14ቱ እንዲሁም 5 ከተሞች የ24 ሰዓት ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል::

የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት መስፋፋት የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ በእጅጉ እንዳሻሻለ የጠቀሱት አስተዳዳሪው፣ ቀደም ሲል ነዋሪዎች ለብርሃን ምንጭነት ኩራዝ ይጠቀሙ ስለነበር በትራኮማ በሽታ ይሰቃዩ እንደነበር አስታውሰዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል መኖር ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ የህብረተሰቡን ጤና ጠብቋል።

በተለይ ሴቶችና እናቶች ምግብ ለማብሰልና እህል ለማስፈጨት ለከፍተኛ ወጪ እና የጤና እክል ይዳረጉ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ኃይልን መጠቀም በመጀመራቸው ኑሯቸውን በቀላልና በዘመናዊ መንገድ መምራት ጀምረዋል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የኃይል ማመንጫው ከ96 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲረጋገጥ አስችሏል። በኤሌክትሪክ ኃይል በሚሰሩ የውሃ ፓምፖች አማካኝነት በርካታ ቀበሌዎች የጉድጓድ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል።

የመልካ ዋከና ኃይል ማመንጫ ጣቢያ  ለቀሪ የወረዳው ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማዳረስ በትጋት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱከሪም፣ ለወረዳው ሁለንተናዊ እድገት እያደረገ ያለውን የማይተካ ሚናም  አመስግነዋል።

Scroll to Top