የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን መልካም ስምና ገፅታ በመጠበቅ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ውጤታማ ሥራዎችን ላከናወኑ አመራሮችና ሠራተኞች ዕውቅና ሊሰጥ እንደሚገባ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኃይል ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተች ነው፡፡
የፕሮጀክት ግንባታዎችን በራስ አቅም የማከናወን ብቃት እያደገ መምጣቱን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ማጠናቀቅ እየተቻለ ነውም ብለዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ለደረሰበት ስኬት የበቃው በተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች እንዲሁም በመንግሥት እልህ አስጨራሽ ትግል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ከተቋሙ ጋር በመተባበር ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጓጉዙ እንደነበር የጠቀሱት ኢንጂነር አሸብር የፀጥታ ዘርፎቹ እና የተቋሙ ሠራተኞች ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር አኩሪ ተግባር ላይ በመሳተፋቸው ሊኮሩ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም በተግዳሮቶች የተሞላ ቢሆንም በመንግሥት እና በተቋሙ የቦርድ አመራር ክትትልና ድጋፍ የላቀ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ወጪ ቆጣቢ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
በበለስ፣ ፊንጫ፣ ህዳሴ እና አይሻ የኃይል ማመንጫዎች እየሰሩ የሚገኙ የተቋሙ ሠራተኞች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ውጤታማ ሥራዎች እያከናወኑ ነው ያሉት ኢንጂነር አሸብር ለዚህም ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በተቋሙ በሁሉም የሥራ ዘርፎች የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮች እና ሠራተኞች የማበረታቻ ዕውቅና ይሰጣል፡፡
በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች ሳቢያ ለጥገና የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን የገለፁት ኢንጂነር አሸብር የተቋሙን ሀብት በእኔነት ስሜት መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በቀጣይ ተቋሙ ተግባራዊ እያደረገው በሚገኘው አዲስ መዋቅር የሠራተኛውን አቅም በማጎልበት የእርካታ ደረጃውን ለማሻሻል እንደሚሰራም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የጠቆሙት፡፡
በተቋሙ ለሦስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የግሪድ ስትራቴጂ በቀጣዩ በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ የገለፁት ኢንጂነር አሸብር አዲስ ለሚቀረፀው የስትራቴጂክ ዕቅድ ሁሉም ሠራተኛ ግብዓቶችን በማቅረብ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

