በለገጣፎ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አጠገብ ያለው የደረቅ ቆሻሻ ማከማቻ አዕዋፋት እንዲሰባሰቡና ተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ አንድ ሪጅን አስታወቀ፡፡
በሪጂኑ የለገጣፎ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ታምራት ፎጊ እንደገለፁት በጣቢያው አቅራቢያ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ በመኖሩ ከትንሽ እስከ ትላልቅ አእዋፋት ምግብ ለመፈለግ ወደ ቆሻሻ ቦታው ይሰባሰባሉ።
ይኽም ከከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጋር በሚያደርጉት ንክኪ ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ እንዲያጋጥም ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታው ከጣቢያው አካባቢ እንዲነሳ ለለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አስተዳደር በደብዳቤ ጥያቄ ቢቀርብም እስከአሁን ድረስ ተግባራዊ ምላሽ አለመሰጠቱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ከኃይል መቋረጥ ባሻገር ይህ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያው በበጋ ወራት የተለያዩ ተቀጣጣይ ቁሶች የሚከማችበት በመሆኑ በአቅራቢው በሚገኘው የኃይል ማከፋፈያ እና የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የእሳት አደጋ ስጋት በመደቀኑ የቆሻሻ ማከማቻ ቦታው በአፋጣኝ እንዲነሳ አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የለገጣፎ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የ24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

