ውሳኔ ካገኙ የፍትኃብሔር ክርክሮች ከ562 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል

ውሳኔ ካገኙ የፍትኃብሔር ክርክሮች ከ562 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች ክርክር ካካሄደባቸው የፍትኃብሔር መዝገቦች 562 ነጥብ 722 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን የተቋሙ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ገለፀ፡፡

‎የመምሪያው ተወካይ ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም በቀለ እንደገለፁት በ2017 በጀት ዓመት በተጀመሩ 188 እና ከ2016 በጀት ዓመት በተላለፉ 144 መዝገቦች ላይ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

‎ክርክር ሲካሄድባቸው ከቆዩት መዝገቦች ውስጥ 68ቱ ውሳኔ ያገኙ ሲሆን 42ቱ ለተቋሙ እንዲሁም 5ቱ ደግሞ በተቋሙ ላይ ተወስነዋል ብለዋል፡፡

‎ቀሪ መዝገቦች በክትትል ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ውሳኔ ከተሰጠባቸው መዝገቦችም ከ562 ነጥብ 72 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት፡፡

‎ከፍትኃብሔር መዝገቦች በተጨማሪ 121 የወንጀል መዝገቦች ላይ ክትትል መደረጉን የጠቆሙት ወ/ሮ መስከረም ከዚህ ውስጥ ውሳኔ ባገኙ ዘጠኝ መዝገብ ተከሳሾች ላይ የገንዘብ እና እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ የፅኑ እስራት ቅጣት መተላለፉንም ተናግረዋል፡፡ 

‎መምሪያው ከከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ስርቆት እና ተቋሙ ከመሬት ይዞታ ግብር ነጻ በሚሆንበት ዙሪያ ከፍትኅ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

‎የማህበረሰብ የእኔነት ስሜት በመፍጠር ከከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ስርቆትን ለመከላከል ከቀበሌ መስተዳድሮች ጋር በጋራ ለመስራት ውል መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

‎በተጨማሪም ከካሳ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በፍ/ቤት ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲቀረፉ እንዲሁም በካሳ ጉዳይ ክርክሮች ላይ ሐሰተኛ ማስረጃ በሚሰጡ የአስተዳድር አካላት፣ በሐሰት ክስ የተጋነነ ብር በሚያስወስኑ ከሳሾች እንዲሁም ያለህጋዊ መብት ክስ እየመሰረቱ በሚከራከሩ ጠበቆች ላይ የሙስና ወንጀል ምርመራ እንዲከናውን ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አቃቤ ሕግ ቢሮ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

‎እንደ ተወካይ ዳይሬክተሯ ገለፃ የሥራ ክፍሉን ሥራ ውጤታማነት ለማሳደግ የመዝገብ ክትትሉን አውቶሜሽን ለማድረግ የሚያስችል ሶፍትዌር የማበልፀግ እንዲሁም የወጡ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣  የአሰራር ሥርዓት ማኑዋሎች እና ፖሊሲዎችን  የማሰባሰብ፣ የማደራጀትና የመፈተሽ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

‎የግብዓት ዕጥረት፣ የተደራጀ የመረጃ አያያዝ እለመኖር እና የካሣ ሕጉ በተቋሙ ካለው የአሠራር ሥርዓት ጋር የተቀራረበ አለመሆን በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ አብራርተዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top