በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት የታዩ ክፍተቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ የአዳማ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ገለፀ።
የጣቢያው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2018 ዕቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
የጣቢያው የጥገና ክፍል ሥራ አስኪያጅ እና የጣቢያው ተወካይ ኃላፊ አቶ ይታየው ቸሩ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት ጣቢያው የ2017 በጀት ዓመት የኃይል ምርት ዕቅዱን ለማሳካት የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በጣቢያው የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን በማሳደግ እንዲሁም ዓመታዊ የትንበያ እና የፍተሻ ጥገና ሥራዎችን በተቀመጠላቸው ጊዜ በማከናወን ዕቅዱን ለማሳካት ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
በራስ ኃይል የጥገና ሥራዎችን ማከናወን መቻል እንዲሁም የእርስ በእርስ የመማማር አቅም እያደገ መምጣት በበጀት ዓመቱ ከታዩ ጠንካራ ጎኖች መካከል እንደሚጠቀሱ በውይይቱ ተመላክቷል፡፡
በጣቢያው ባለሙያዎች የተርባይን ቅየራ ሥራ መከናወኑ፣ የ33 ኪሎ ቮልት መስመር እና ሰርኪዩት ብሬከር እንዲሁም የኮሙዩኒኬሽን ፋይበር መጠገን መቻሉ የበጀት ዓመቱ የጣቢያው ስኬቶች መሆናቸውንም ነው አቶ ይታየው ያብራሩት፡፡
በመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት ምክንያት 6 ተርባይኖች ለወራት መቆማቸው እንዲሁም የተጋነነ ዕቅድ መያዙ ለአፈፃፀሙ ዝቅ ማለት እንደምክንያት በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል።
የሥራ ላይ መሳሪያዎች በወቅቱ አለመቅረብ እና የተሸከርካሪ እጥረት መኖር እንዲሁም ወደ ተርባይን የሚያስኬዱ መዳረሻ መንገዶች ጥገና አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን በጣቢያው የጥገና ሥራዎች ላይ ተግዳሮት መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ይታየው ገለፃ በ2017 በጀት ዓመት የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም በትብብር ይሰራል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





