የገፈርሳ – ሙገር ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር የማዘመን ሥራ ከ86 በመቶ በላይ መጠናቀቁን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ አንድ ሪጅን መምሪያ አስታወቀ።
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ገዛኸኝ እንዳስታወቁት መስመሩ ለረጅም ዓመት አገልግሎት በመስጠቱ በተደጋጋሚ ለሚከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት በመሆኑ ነባሩን በአዲስ ኮንዳክተር የመቀየር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል::
በ1975 ዓ.ም ለሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካው ኃይል ለማቅረብ የተዘረጋው የገፈርሳ-ሙገር የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር በአሁኑ ወቅት ለደርባና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሁም በአካባቢው ለሚገኙ ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ቀደም ሲል እስከ ሐበሻና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ድረስ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ይህ መስመር፣ በእርጅና ምክንያት ያጋጥመውን ችግር መቅረፍ የሚያስችል የማሻሻያ ሥራ እየተከናወነለት ነው።
እንደ አቶ ደረጀ ገለፃ የማሻሻያ ሥራው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የፋብሪካዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ያግዛል።
አጠቃላይ ርዝመቱ 80 ኪሎ ሜትር እና 242 የታወር ብዛቶች ያሉት የገፈርሳ-ሙገር ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር የማሻሻያ ሥራ በሦስት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከናወን መሆኑንና ከዚህ ውስጥ 70 ኪሎ ሜትር ያህሉን ማጠናቀቅ እንደተቻለ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”