የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ ዓመታዊ አፈፃፀሙን እየገመገመ ነው

የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ ዓመታዊ አፈፃፀሙን እየገመገመ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር ቦርድ የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት  የዕቅድ አፈፃፀም በስካይ ላይት ሆቴል መገምገም ጀምሯል።

ግምገማው ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በሰው ኃይል ልማት፣ በፋይናንስ፣ በኃይል ማመንጨት፣ በማስተላለፊያ፣ በማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታና የጥገና ሥራዎች እንዲሁም በሪፎርም ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የበጀት ዓመቱን የአስራ ሁለት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ያቀረቡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ተቋሙ አራቱን የስትራቴጂክ  የትኩረት መስኮች ለማሳካት በርካታ ሥራዎች አከናዉኗል።

በበጀት ዓመቱ በኃይል ማመንጨት፣ ማከፋፈል፣ ማስተላለፍ እና ሽያጭ እንዲሁም በዋና ዋና ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ አበረታች ለውጦች መታየታቸውን ጠቁመዋል።

በዘርፉ ለዘመናት የተከማቸውን ዕዳ በተወሰነ ደረጃ ወደ ሌላ ተቋም በማዘዋወር የዘርፉን ዕዳ ማቃለል መቻሉን የጠቀሱት ኢንጂነር አሸብር ለ12 ዓመታት ሳይከለስ የቆየውን የኤሌክትሪክ ታሪፍ በማሻሻል ተቋሙ የተሻለ ገቢ እንዲኖረው ተደርጓልም ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የተቋሙን የአሰራር ሥርዓት ለማዘመንና ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው የጠቀሱት።

በበጀት ዓመቱ የኃይል ምርት እና ሽያጭ ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዕድገት ማስመዝገቡንም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለፁት።

በበጀት ዓመቱ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ መሰራቱን ኢንጅነር አሸብር ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶችን ክትትል ዲጂታል በሆነ የአሰራር ሥርዓት ማዘመን መቻሉን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከፕሮጀክቶች የሚገኙ ትርፍ ምርቶችን ወደ ገቢ ለመቀየር ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው የሲስተም ኦፕሬተሮች ጋር በጥገና እና ኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን አንስተዋል።

ሠራተኞችን በውስጥ አቅም ማብቃት መቻሉ እና የመለዋወጫ አቅርቦት በተለያዩ አማራጮች እንዲገዙ መደረጉ እንዲሁም ቆመው የነበሩ ዩኒቶች ተጠግነው ሥራ መጀመራቸው በበጀት ዓመቱ የታዩ የለውጥ ሥራዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

አንድ አጠቃላይ የኃይል መቋረጥ በግሪድ ሥርዓቱ ላይ ማጋጠሙ፣ በግዥ የአሰራር ሥርዓቶች የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ድክመት መታየቱ፣ የመቆጣጠሪያ ሥርዓቶችን የማዘመንና ወጥነት ያለው ሥራ አለመሰራቱ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮችን በተሟላ ሁኔታ መተግበር አለመቻሉ በበጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውም ኢንጅነር አሸብር ተናግረዋል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top