“ተቋሙ ያስመዘገባቸው ውጤቶች በመንግሥት ድጋፍ የመጡ ናቸው”  አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

“ተቋሙ ያስመዘገባቸው ውጤቶች በመንግሥት ድጋፍ የመጡ ናቸው”  አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት ያስመዘገባቸው ውጤቶች በመንግሥት ድጋፍና ክትትል የተገኙ መሆናቸውን የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ላይ በስካይ ላይት ሆቴል ግምገማ አካሂዷል።

ግምገማው ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በሰው ኃይል ልማት፣ በፋይናንስ፣ በኃይል ማመንጨት፣ በማስተላለፊያ፣ በማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታና የጥገና ሥራዎች እንዲሁም በሪፎርም ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የቦርድ ሰብሳቢው አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በግምገማው ወቅት እንደገለፁት የተቋሙን የ2017 ዕቅድ አፈፃፀም መታየት ያለበት ከቁጥሮች በላይ በመመዘን ነው።

መንግሥት የተቋሙን የዕዳ ጫና በማቃለል እንዲሁም የታሪፍ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ አቅጣጫ በማስቀመጥ አወንታዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ተናግረዋል።

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በፕሮጀክት ግንባታ አፈፃፀም፣ በኦፕሬሽን እና በኃይል ሽያጭ ዘርፍ እንዲሁም በሪፎርም ሥራዎች ላይ መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ በኃይል ልማት ዘርፉ የሚገነቡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በቦርዱ ይሁንታ ሳያገኙና የጋራ መግባባት ላይ ሳይደረስባቸው ግንባታቸው እንደማይጀመርም ነው የገለፁት።

የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ በበኩላቸው እንደገለፁት በሀገር ደረጃ እንደ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ትልቅ ሀብት የፈሰሰበት ተቋም የለም።

አዲሱ የተቋሙ ስትራቴጂክ ዕቅድ የሚቀጥሉትን አምስት ዓመታት የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎች ሊመልስ የሚችል መሆን እንዳለበትም ነው በአፅዕኖት የተናገሩት።

እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለፃ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ተይዘው ላልተጠናቀቁ ሥራዎች ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችል አሰራር መዘርጋት አለበት።

የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ አባል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ የተገኘው ውጤት ለኃይል ሽያጭ ዕድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።

ከኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት ጋር በተያያዘ ለቦርድ አመራሩ በየጊዜው ሪፖርት የሚቀርብ ቢሆንም የቅርብ ክትትል ተደርጎ አፈፃፀማቸውን መገምገም ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየታቸውን የጠቆሙት አቶ መላኩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መስተዳድር አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ አባል የመከላከያ ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይሻ መሐመድ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ወይም የራስ ኃይል በኩል የተሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባል አንስተዋል።

የረጲ የደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያን ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የጥገና ሥራው አዋጭነቱ መታየት እንዳለበት አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የሥራ ላይ ደህንነት መሳሪያዎችን አቅርቦት ከማሻሻል ባለፈም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top