የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ ተቋማቱ በቅንጅት እየሠሩ ነው

የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ ተቋማቱ በቅንጅት እየሠሩ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመልካ ዋከና ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዙሪያ የሚገኙ ቀበሌዎችን የኃይል ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ተገለፀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመልካ ዋከና የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ እንደገለፁት ግድቡ በሚሰራበት ወቅት ከቦታቸው እንዲነሱ ለተደረጉ ነዋሪዎች የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት አስፈልጓል።

በዚህም መነሻነት ተቋሙ ከአሁን ቀደም ለአካባቢው ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የመንገድ ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በህብረተሰቡ ሲነሳ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎች ለመመለስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ገልፀዋል።

በዚህም ሁለቱ ተቋማት በ40/60 የወጭ መጋራት አሰራር መሠረት ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ በጣቢያው ዙሪያ ለሚገኙ 12 ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራው የአካባቢው ማህበረሰብ በጣቢያው ላይ ያለውን የእኔነት ስሜት አሳድጓል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኦሮሚያ ገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ሁሴን ቴሲሶ በበኩላቸው ተቋማቱ በጣቢያው ዙሪያ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም 12 ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከታቅደው እስከ አሁን 8 ቀበሌዎችን በከፊል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት ኃላፊው ቀሪዎቹን በአጭር ጊዜ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በሁሉም ቀበሌዎች ከሚተከሉ ትራንስፎርመሮች 46 በመቶ፣ የመካከለኛ መስመር ምሰሶ ተከላ 82 በመቶ እንዲሁም የዝቅተኛ መስመር ምሰሶ ተከላ ሥራ 72 በመቶ መጠናቀቁን አቶ ሁሴን አስረድተዋል።

አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከ60 በመቶ በላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ በማመንጫ ጣቢያው እየተከናወነ ያለው የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራ አገልግሎቱ እንደ ሀገር የኃይል ተደራሽነት ሽፋንን እና የገቢ አሰባሰቡን ለማሳደግ የያዛቸውን ዕቅዶች ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማሳደግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየና የመረጃ ባለቤት እንዲሆን በማስቻል የራሱን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት የተናገሩት የሥራ ኃላፊዎቹ ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን ሁለቱ ተቋማት ከማህበረሰቡና ከመስተዳድር አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በቀበሌዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ከተያዘው ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ውስጥ 60 በመቶው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀሪው 40 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሸፈን ነው።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top