የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚደግፍ የኃይል አቅርቦትን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መስራት ይገባል

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚደግፍ የኃይል አቅርቦትን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መስራት ይገባል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2018 በጀት ዓመት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚደግፍ የኃይል አቅርቦትን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንዲሰራ የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አሳሰቡ።

የሥራ አመራር ቦርድ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት የፊዚካል እና የበጀት ዕቅድ ገምግሟል፡፡

የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለሥራ አመራር ቦርዱ ያቀረቡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ተቋሙ በአደረጃጀት፣ በአሰራር እና በሰው ሀብት ልማት እንዲሁም የፋይናንስ ቁመናውን በማሳደግ ዙሪያ ተከታታይ የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡

ከኃይል መሠረተ ልማት ስርቆት ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ገልፀዋል።

በኃይል መሠረተ ልማት ስርቆት ሳቢያ በተቋሙ ላይ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ ከመሰረቱ ለማስቀረት ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ዘላቂ ግንኙነት የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡

እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ በበጀት ዓመቱ ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ አሰራር በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በጥራት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡

ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት እንዲችል የኃይል ማመንጨት፣ ማስተላለፍ እና ማከፋፈል አቅምን ለማሳደግ እንደሚሰራም ነው የገለፁት፡፡

የፕሮጀክቶች ግንባታ፣ ኦፕሬሽን እና ኮርፖሬት ሰርቪስ ሥራዎች የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ የአሰራር ሥርዓቶችን ማዘመን እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የፋይናንስ ቁመናን ከማሳደግ አኳያ የኃይል ብክነትን የመቀነስ፣ የአሰራር ቅልጥፍናን የማሻሻል፣ ከውጭ የኃይል ሽያጭ እና ከሌሎች የሚገኝ ገቢን በአግባቡ የመሰብሰብ እንዲሁም የቢዝነስ አማራጮችን የማስፋት ሥራዎች እንደሚሰሩም ነው የጠቆሙት፡፡

የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚደግፍ የኃይል አቅርቦትን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

የሰለጠነ የሰው ኃይል ስብጥርን ከማመጣጠን እንዲሁም ሀብትን በተገቢው መንገድ ከማስተዳደር አንፃር በትኩረት መሰራት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት፡፡

የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ አባል የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፈቃዱ ደግፌ በበኩላቸው ተቋሙ የፋይናንስ ቁመናው እንዲሻሻል በማድረግ የዕዳ ጫናዎቹን በራሱ ገቢ ለመሸፈን ዕቅድ ይዞ መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top