ተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም መገምገም ጀመረ

ተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም መገምገም ጀመረ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራሮችና ሠራተኞች የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም በተቋሙ የስብሰባ አዳራሽ መገምገም ጀምረዋል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የግምገማ መርሃ-ግብሩን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት በጀት ዓመቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ለዓለም ህዝብ የተበሰረበት ነው።

ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

የግድቡ መጠናቀቅ የሁሉም የተቋሙ የሥራ አመራሮች እና ሠራተኞች እንዲሁም የመንግሥት ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በተቋሙ የ12 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም እና ተቋሙን በቀጣይ ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል።

በ2018 በጀት ዓመት የበለጠ ውጤት ለማምጣት በሚቻልባቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በአፈፃፀም ውይይቱ ላይ ሁሉም አመራሮችና ሠራተኞች ለተቋሙ ውጤታማነት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሳስበዋል።

ግምገማው በተቋሙ የስትራቴጂክ ዕቅድ የትኩረት መስኮች በሆኑት የአስተዳደርና የኦፕሬሽን ልህቀት፣ የማይበገርና አስተማማኝ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የፈጠራና የዲጂታል ሽግግር እንዲሁም በሰው ሃብት ልማት ላይ ባለፉት 12 ወራት በተከናወኑ አበይት ተግባራት ላይ ያተኩራል።

በአፈፃፀም ግምገማው ላይ የተቋሙን የ12 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች እና ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሔዳል ተብሎም ይጠበቃል።

የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ከመጀመሩ አስቀድሞ ተቋሙ በጀት ዓመቱ በህይወት ላጣቸው ሠራተኞች የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top