ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጠናከር የኃይል አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራች ነዉ

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጠናከር የኃይል አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራች ነዉ

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጠናከር በማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ያለውን 54 በመቶ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት በሚቀጡልት ዓመታት ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የሀገሪቱን የኃይል ልማት ዘርፍ ማሻሻል እና ማዘመን ላይ ያተኮረ ውይይት ከስራ ተቋራጮች ጋር አካሂደዋል፡፡

በዘርፉ የፕሮግራም ሁለት ዳይሬክተር አቶ ደስታለም ኃይሉ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በኃይል አማራጭ ላይ እያከናወነች ያለውን መጠነ ሰፊ ስራ ጠቅሰው የኃይል ተደራሽነት ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስራ ኃላፊዎች ለስራ ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን በጨረታ አሸንፈው የብድር አገልግሎት በሚያገኙባቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያያ የሚሆኑ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በዓለም ባንክ የግዢ ባለሙያ አቶ አማረ አሰፋ ባቀረቡት ሰነድ ባንኩ በኢነርጂ፤ በትምህርት፤ በፆታ፤ በአየር ንብረት ዘርፎች እና መሰል ጉዳዮች ላይ ለተበዳሪዎች የራሱን ፕሮግራም ቀርፆ እንደሚሰራ ገልፀው በኃይል ልማት ዘርፍ ላይ የሚሳተፉ የስራ ተቋራጮች ስለባንኩ ማወቅ ያለባቸዉን የአሰራር ስርዓቶች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ አማረ ገለፃ ባንኩ በዓለም ላይ በ327 ቢሊዮን ዶላር 1 ሺህ 819 ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው ከእነዚህ ፕሮጀክቶች 41 በመቶዉ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ላይ እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በፕራይም አንድ ሊያስገነባቸዉ ያሰባቸዉን ስድስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ጨምሮ ተቋሙ በማከፋፈያ ጣቢዎች እና ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ እየሰራቸው ያለውን የማዘመን እና የማስፋፋት ስራዎችን አስመልክቶ በተወካዩ አቶ ታደሰ ብሩ ሰነድ ቀርቧል፡፡

መድረኩ በዋናነት ፕሮጀክቶች በታለመላቸዉ ጊዜ እና ጥራት ተጠናቀው አገልግሎት ላይ እንዲዉሉ የግዥ ሂደት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ተጫራቾች፤ አቅራቢዎች እና ፍላጎቱ ያላቸው ተቋማት በቀረበው ሰነድ ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ እና የገበያ ዕድሉን ለማስፋት ያለመ መሆኑን በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

Scroll to Top