የአላማጣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የጣቢያው የኦፕሬሽንና ጥገና ባለሙያ ገለፁ።
ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ አሰፋ እንደገለፁት ጣቢያው ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እየሰጠ የቆዬ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በኦፕሬሽን እና ጥገና ሥራዎች ላይ አሉታዊ ጫና እየተፈጠረ ይገኛል።
የጣቢያው የመቆጣጠሪያ ሥርዓት የአገልግሎት ዘመኑን ያጠናቀቀ በመሆኑ ለተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና ብልሽት እየተዳረገ እንደሚገኝም ነው ያነሱት።
እንደ ባለሙያው ገለፃ የጣቢያውን አቅም ለማሳደግና ደህንነቱን አስተማማኝ አድርጎ ለማስቀጠል የዘመናዊ ስዊችጊር ቅየራ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል።
እስከ 140 ሜጋ ዋት ድረስ ኃይል የመሸከም አቅም ያለው የአላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ለሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ኤሌክትሪክ በማቅረብ በኩል ድርሻው የጎላ ነው።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ሁለት ባለ 63 ሜጋ ቮልት አምፔር አውቶ ትራንስፎርመሮች እና ሁለት ባለ 20 ሜጋ ቮልት አምፔር እንዲሁም አንድ ባለ 25 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው አምስት ትራንስፎርመሮች አሉት።
ጣቢያው ከባህር ዳር ኃይል ተቀብሎ በ230 ኪሎ ቮልት ለኮምቦልቻ፣ መኾኒና አሸጎዳ እንዲሁም በ66 ኪሎ ቮልት ለማይጨው፣ ሰቆጣና ላሊበላ ኤሌክትሪክ እየሰጠ ይገኛል፡፡
ባለሙያው እንደገለፁት ጣቢያው ካሉት አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች መካከል አንዱ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ቀሪዎቹ ሦስት መስመሮች ለኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ዝግጁ ተደርገው ተቀምጠዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



